የባህር በር – የከፍታ መስመር

You are currently viewing የባህር በር – የከፍታ መስመር

• የባሕር በር የሌላቸው ሀገራት ምንም እንኳን ብዙ የተፈጥሮ ሃብቶች ቢኖሯቸውም የዓለምን የባሕር ንግድ ስርዓት ማግኘት ባለመቻላቸው ለተለያዩ ኪሳራዎች እንደሚጋለጡ ተጠቁሟል

ተፈጥሮ ለሀገራት የተለያዩ ፀጋዎችን ለግሳለች፡፡ ለአንዳንዶቹ የባሕር በርን፣ ለአንዳንዶቹ ነዳጅን፣ ለአንዳንዶቹ  አልማዝን የመሳሰሉ ውድ ሀብቶችን ትቸራቸዋለች፡፡ ከዚህ ሁሉ ግን  ለሀገራት የባሕር በር በጣም ወሳኙ ሀብት ነው ሊባል ይችላል፡፡

“ባሕር እና ሥልጣ፡- የዓለም የባሕር ታሪክ” (The Sea and Civilization A Maritime History of the World) በሚል ርዕስ እ.ኤ.አ ሰኔ 2015 የባሕር ታሪክ ተመራማሪ የሆኑት ሊንከን ፔይን ባሳተሙት መፅሐፍ ላይ እንደሰፈረው የባሕር በር ለሀገራት ለምግብና መጓጓዣ ብቻ ሳይሆን የንግድ መስመሮችን፣ የኃይል አቅርቦትን አልፎ ተርፎም የመከላከያ አቅምን ማጠናከሪያ ማማ፣ ክንድን ማፈርጠሚያ ሰገነት ሆኖ በማገልገል የሀገራት ከፍታ መለኪያ እስከመሆንም ደርሷል፡፡

ባሕር ከመጓጓዣነት ባሻገር ሰፊ የብዝሃ ህይወት መኖሪያ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ሌላ ሀብትና ሌላ ዕድልን የሚፈጥር ነው፡፡ ባሕር በሀገራት መካከል እንደ ድልድይ በማገልገልም ልዩ ጥቅምን ይሰጣል። በተለይ በኢኮኖሚ ብልፅግና እና በዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ ተጽዕኖ ከማሳደር አንፃር የባሕር ተደራሽነት ያላቸው ሀገራት ወደብ ከሌላቸው ሀገራት ጋር ሲነፃፀሩ በጣም ከፍ ያለ ተጠቃሚነት እንዳላቸውም ሊንከን ፔይን በመፅሐፋቸው ጠቅሰዋል፡፡

ከሁሉም በላይ ፔይን የሀገራት የሥልጣኔ ከፍታና ዝቅታ ከባሕር ጋር እንዴት እንደሚቆራኝ በግልጽ አስቀምጠዋል፡፡ በተለይም የዓለማችን ስልጣኔ ዞሮ ዞሮ መነሻውና መድረሻው ባሕር ነው ይላሉ፡፡ ታዲያ ዓለማችን ለሁሉም ሀገራት ባሕር የላትምና ሁሉም ተጠቃሚ መሆን እንዲችል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እ.ኤ.አ በ1994 “የተባበሩት መንግስታት የባሕር ህግ ስምምነት” (United Nations Convention on the Law of the Sea) የተሰኘ የባሕር ሕግን ስራ ላይ አውሏል። ይህ ሕግ በ168 ሀገራት የተፈረመ ነው። ይህም በጣም ተቀባይነት ካላቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች አንዱ ተደርጎም ይወሰዳል፡፡

በመሆኑም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የባሕር ሕግ አንቀጽ 69 ንዑስ አንቀጽ 1 እስከ 5 የባሕር በር የሌላቸው ሀገራት በአካባቢያቸው ካለው ባሕር የተፈጥሮ ሀብት እኩል የመጠቀም መብት እንዳላቸው በግልፅ ያስቀምጣል፡፡ ይህም ዓሳ ማጥመድን እና በባሕር ውስጥ ያሉ የተፈጥሮ ሀብቶችን ፍለጋን ይጨምራል፡፡ ሌሎች ከባሕር ተፈጥሮ ሀብት ጋር የተያያዙ ሀብቶች ተጠቃሚነት መብትንም ያካትታል፡፡ በዚሁ ሕግ በአንቀጽ 125 ንዑስ አንቀጽ 1 እንደተቀመጠው የባሕር በር የሌላቸው ሀገራት በአካባቢያቸው ያለውን ባሕር የመጠቀም እና የመሸጋገር ዓለም አቀፍ መብት እንዳላቸውም በጉልህ ሰፍሯል፡፡

ታዲያ ይህ መብት የባሕር በር በሌለው ሀገር፣ የባሕር በር ባለቤት በሆነው ሀገር እና በቀጣናው መካከል በሚደረግ ስምምነት ሊፈጸም እንደሚገባም በንዑስ አንቀጽ 2 ላይ ተቀምጧል፡፡ አንቀጽ 27 ንዑስ አንቀጽ 1 ላይ ደግሞ እነዚህ የባሕር በር የሌላቸው ሀገራት በሰምምነት ከተደረገ የተለየ የአገልግሎት ክፍያ ከሌለ በስተቀር ለተገለገሉበት ባሕር ምንም ዓይነት የትራፊክ ታክስ ወይንም ሌላ ክፍያ እንደማይጠየቁም ተደንግጓል፡፡

እነ አሜሪካ፣ ሩሲያ፣ ቻይና፣ ጃፓንና ብዙዎቹ የአውሮፓና የላቲን አሜሪካ ሀገራት ለኢኮኖሚ ጥንካሬያቸው ብቻ ሳይሆን ለደኅንነታቸውም ቢሆን ወሳኝ ሀብት የባሕር በር ወይም ወደባቸው ስለመሆኑም ዣን ፖል ሮድሪግ እ.ኤ.አ ግንቦት 6 ቀን 2020 The Geography of Transport Systems በሚል ርዕስ ባሳተሙት መፅሐፍ ላይ ሰፍሯል፡፡

እ.ኤ.አ. በ1963 በተቋቋመው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ወይም በአሁኑ አጠራሩ የአፍሪካ ህብረት (AU) ቻርተር መግቢያ ላይ በግልፅ እንደሰፈረው የአፍሪካ ሀገራት የባሕር በር የሌላቸውን ጨምሮ የባሕር ላይ ተጠቃሚ የመሆን መብት እንዲኖራቸው በተለይ የባሕር በር የሌላቸው ሀገራት በባሕር ላይ የመጠቀም መብታቸው እንዲጠበቅ እውቅና ይሰጣል፡፡

በቻርተሩ ላይ በሰፈረው መረጃ መሰረት በአፍሪካ ሁኔታ በርካታ የባሕር በር የሌላቸው ሀገራት አሉ። ሀገራቱ ምንም እንኳን ብዙ የተፈጥሮ ሃብቶች ቢኖሯቸውም የዓለምን የባሕር ንግድ ስርዓት ሙሉ በሙሉ ማግኘት ባለመቻላቸው ለተለያዩ ኪሳራዎች ይጋለጣሉ፡፡ በመሆኑም የባሕር በር የሌላቸው ሀገራት የባሕር በር ካላቸው ሀገራት መጠቀም የሚችሉበትን መርሆ ከዓለም አቀፍ ሕግጋት ጋር በማመሳከር ቻርተሩ በመርህ ደረጃ አስቀምጧል፡፡

ዓለም አቀፉ የንግድ ድርጅት እ.ኤ.አ ህዳር 10 ቀን 2021 ይፋ ባደረገው መረጃ መሰረት በዓለም 44 ወደብ አልባ ሀገራት አሉ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ 31 ያህሉ ደሃ ናቸው፡፡ 13ቱ ደግሞ ከድህነትም በታች ሲሆኑ መገኛቸውም አፍሪካ ናት፡፡ ዋና መቀመጫውን ኒው ዮርክ ያደረገውና ቤስት ዲፕሎማትስ የተሰኘው ገፀ ድር የካቲት 26 ቀን 2024 ይፋ ባድገው መረጃ ደግሞ ሀገራቱን ወደ 16 ከፍ ያደርጋቸዋል፡፡ ቦትስዋና፣ ቡሩንዲ፣ መካከለኛው አፍሪካ፣ ቻድ፣ ሌስቶ፣ ማላዊ፣ ማሊ፣ ኒጀር፣ ዝምባቡዌ፣ ሩዋንዳ፣ ስዋዝላድ፣ ኡጋንዳ፣ ቡርክናፋሶ፣ ዛምቢያ ኢትዮጵያ እና ደቡብ ሱዳን በማለት፡፡

ጥቂት የማይባሉ የባሕር በር የሌላቸው ሀገራት በስትራቴጂክ ወዳጅነት እና በዲፕሎማሲያዊ ጥረት ችግሮቻቸውን ማቃለል ችለዋል፡፡ በዓለም ላይ ያሉ በርካታ ሀገራት ወደብ ከሌላቸው መንግስታት ጋር ድንበር ይጋራሉ።

ለአብነትም በመካከለኛው አውሮፓ የምትገኘው ጀርመን:- ኦስትሪያን፣ ስዊዘርላንድን እና ሉክሰምበርግን ጨምሮ በርካታ ወደብ ከሌላቸው ሀገራት ጋር ድንበር ትጋራለች። ምንም እንኳን ጀርመን ራሷ የሰሜን ባሕር እና የባልቲክ ባሕር መዳረሻ ቢኖራትም ወደብ የሌላቸው ጎረቤቶቿ ዓለም አቀፍ የንግድ መስመሮችን ለማግኘት በወደቦቿ እና በመሠረተ ልማት አውታሮች እንዲጠቀሙ ታደርጋለች።

ለምሳሌ ስዊዘርላንድ ምንም እንኳን የባሕር በር አልባ ብትሆንም በጀርመን ወደቦች እንደ ሃምበርግ እና ብሬመን የመሳሰሉትን ወደቦች ለዕቃ ማጓጓዣ ትጠቀምባቸዋለች። በተመሳሳይ፣ ኦስትሪያ የጀርመን ወደቦችን ለዓለም አቀፍ ንግዷ በተለይም በራይን-ዳኑብ ኮሪደር በኩል ለመጓጓዣ ቁልፍ የሆነውን የውሃ መንገድ ትጠቀማለች። በመሆኑም ጀርመን እና የባሕር በር አልባ ጎረቤቶቿ በአውሮፓ ህብረት እና በአውሮፓ ኢኮኖሚ ማዕቀፍ ውስጥ በሚደረጉ ስምምነቶች ውስጥ በመሳተፍ ወደብን በጋራ ይጠቀማሉ ይላል  የአውሮፓ ህብረት እ.ኤ.አ  2020 ይፋ ያደረገው መረጃ።

በደቡብ አሜሪካም ፓራጓይ እና ቦሊቪያ ወደብ የሌላቸው ድንበር ተጋሪ ሀገራት ናቸው። በሁለቱ ሀገራት መካከል ከሚደረጉት የሁለትዮሽ ስምምነቶች በተጨማሪ በደቡብ አሜሪካ የሚገኘው የክልላዊ የንግድ ቡድን የሆነው ሜርኮሱር፣ በእነዚህ ወደብ አልባ ሀገራት በጎረቤቶቻቸው መካከል በሰጥቶ መቀበል መርህ ላይ የተመሰረተ የንግድ ልውውጥ እንዲኖር አድርጓል፡፡

በአፍሪካ ለአብነትም ዛምቢያ እና ዚምባብዌ ወደብ አልባ ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ በደቡብ አፍሪካ የሚገኘው የደርባን ወደብ ለእነዚህ ሁለት ወደብ ለሌላቸው ሀገራት የንግድ ልውውጥን በማሳለጥ ረገድ ወሳኝ ሚና እየተጫወተ ነው፡፡ በተለይ ዛምቢያ ከደቡብ አፍሪካ ጋር የረጅም ጊዜ ስምምነት አላት፤ በሞዛምቢክ የሚገኘውን የቤይራ ወደብንም እንደ መሸጋገሪያ ማዕከልነት ትጠቅማለች። ለዚህ ደግሞ የደቡብ አፍሪካ ማህበረሰብ ልማት ማህበር ድርሻው ከፍ ያለ ነው፡፡

በእስያ ኔፓል ወደብ የሌላት ሀገር ናት፡፡ ከህንድ ጋርም ድንበር ትጋራለች። ኔፓል እንደ ኮልካታ ያሉ የህንድ ወደቦችን በመጠቀም የባሕር ላይ ንግድን ታከናውናለች፡፡ ሁለቱ ሀገራት ዓለም አቀፍ ህግጋትን እና በተለይ ሰጥቶ መቀበል መርህን በመተግበር ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡ እንደ ኔፓል እና ህንድ ወይም ዛምቢያ እና ደቡብ አፍሪካ ያሉ የሁለትዮሽ ስምምነቶች  የባሕር ላይ መዳረሻ ወይም ወደብ ለሌላቸው ሀገራት ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር ወሳኝ ተሞክሮዎች ናቸው።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review