AMN- ህዳር 11/2017 ዓ.ም
የብሄሮች ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ቀን ህብረብሄራዊነትን የማጎልበት አላማ እንዳለው የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ቡዜና አልከድር አስገነዘቡ ፡፡
19ኛው የኢትዮጵያ ብሄሮች ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ቀን በዓል የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት እና ፓናል ውይይት በአዲስ አበባ ምክር ቤት እና በጨፌ ኦሮሚያ ትብብር በአዲስ አበባ ከተማ እየተካሄደ ነው።
አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ቡዜና አልከድር የብሄሮች ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ቀን በብዝሃነት ላይ የተመሰረተ ፌዴራሊዝም እንዲዳብር በማድረግ ህብረብሄራዊነትን ማጎልበት አላማው ነው፣ይህ ይሆን ዘንድ በአዲስ አበባ ከተማ ደረጃ የተለያዩ ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛል ብለዋል።
እውነተኛ ፌዴራሊዝምን በማጎልበት የህዝቦች ፍትሃዊ ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ የተለያዩ ውይይቶች ተካሂደዋል፣ተጨባጭ ስራዎችም መከናወናቸውን አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ቡዜና ተናግረዋል።
አዲስ አበባ ከተማ የህብረብሄራዊ መገለጫ ነች፣በጋራ የመልማት እሳቤን ይዛ እየሰራች ትገኛለችም ብለዋል።
እውነተኛ ፌዴራሊዝምን ለማስረጽ እና ጠንካራ ሀገር ለመገንባት እጅ ለእጅ ተያይዘን መስራት እንደሚገባም ገልጸዋል።
የጨፌ ኦሮሚያ አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ሰዓዳ አብዱረህማን፣ህዝቦቿን የምትመስል ሀገር ለመገንባት በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።
ሁሉም በእኩልነት እና ፍትሃዊነት የሚኖሩባት ሀገር ለመገንባት በሚደረግ ጥረት ዉስጥ የኢትዮጵያ ብሄሮች ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ሚና የላቀ መሆኑን ገልጸዋል።
“ሀገራዊ መግባባት ለህብረብሄራዊ አንድነት” በሚል መሪ ሀሳብ እየተካሄደ ባለው መድረክ የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ቡዜና አልከድር፣የጨፌ ኦሮሚያ አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ሰዓዳ አብዱረህማን፣በኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት በምክትል ፕሬዜዳንት ማዕረግ የሸገር ከተማ ከንቲባ ዶክተር ተሾመ አዱኛ እና ሌሎች አመራሮች ተገኝተዋል።