የብልፅግና ፓርቲ በከተሞች መሰረተ ልማት ዘርፍ መነቃቃት እንዲፈጠር አስችሏል-አቶ ጌቱ ወዬሳ

You are currently viewing የብልፅግና ፓርቲ በከተሞች መሰረተ ልማት ዘርፍ መነቃቃት እንዲፈጠር አስችሏል-አቶ ጌቱ ወዬሳ

AMN-ጥር 18 /2017 ዓ.ም

የብልፅግና ፓርቲ በቀድሞው አተያይ ከተሞችን የገጠሩ ጥገኛ አድርጎ የማሰብ ዝንባሌዎችን በማስቀረት በከተሞች መሰረተ ልማት ዘርፍ መነቃቃት እንዲፈጠር ማስቻሉን በብልፅግና ፓርቲ የሀረሪ ክልል ቅርንጫፍ ፅ/ቤት ኃላፊ አቶ ጌቱ ወዬሳ ገለፁ።

በሀረሪ ክልል ባለፉት የለውጥ ዓመታት ህዝቡን የሚመጥኑ በተለይ ከነዋሪው ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ላላቸው የልማት ስራዎች ትኩረት በመስጠት እየተሰራ እንደሚገኝ አቶ ጌቱ ወዬሳ ገልፀዋል።

በቀድሞው አተያይ ከተሞችን የገጠሩ ጥገኛ አድርጎ የማሰብ ዝንባሌዎች እንደነበሩ ያስታወሱት አቶ ጌቱ፣ ፓርቲው ይህን መሰሉን ምልከታ በማስቀረት ገጠሩንና ከተማን በመሠረተ ልማት እንዲተሳሰሩና የተሳለጠ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርግ ፈጣን ልማት እንዲኖር ፖሊሲ እና የህግ ማዕቀፍ በማውጣት በዘርፉ መነቃቃት እንዲፈጠር ማስቻሉን ገልፀዋል።

በዚህም የሀረር ከተማን ለመኖሪያ ብቻ ሳይሆን፤ ለስራ የተመቸች ውብ፤ምቹ እና ማራኪ ከተማ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

በተለይ ለከተማ መሰረተ ልማት ትኩረት በመስጠት ከተማዋና ህዝቡን የሚመጥኑ፤ ከነዋሪው ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያላቸው ፕሮጀክቶችን በአጭር ግዜ ጀምሮ በማጠናቀቅ አበረታች ውጤቶች ማስመዝገብ መቻሉን አክለዋል።

በከተማው ብሎም በጁገል የተከናወኑ የኮሪደር እና የአረንጓዴ ልማት ስራዎች ለነዋሪው ፈታኝ የነበሩ አካባቢዎች እንዲፀዱ በማድረግ ሰዎች ተቀምጠው የሚጨዋወቱባቸው ንፁህ እና በብርሀን የተሞሉ እንዲሆኑ ማስቻላቸውንም በማሳያነት ጠቅሰዋል።

በተለይ ሀረር የቱሪዝም መዳረሻ ከተማ እንደመሆኗ በከተማው እየተፈጠሩ የሚገኙ ለእግረኞች የተመቹ መንገዶች የነዋሪውን ደህንነት ከማረጋገጥ ባሻገር ለቱሪስቶች እንቅስቃሴ የተመቹ በመሆናቸው የቱሪስት ፍሰቱ እንዲጨምር ማስቻሉን አክለዋል።

ለውጡን ተከትሎ በከተማው እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ስራዎች ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ዘርፉን ከማጠናከር ባለፈ በሀረር ከተማ ቀድመው የነበሩ ችግሮችን በመቅረፍ፤ከተማው በፕላን እና ስርዓት እንዲመራ በማድረግ፤ ከተማዋን የሚመጥን ዕድገት እንዲመዘገብ እያስቻሉ እንደሚገኙም ጠቁመዋል።

ፓርቲው በቀጣይ ግዜያትም በክልሉ በማህበራዊ፤ ኢኮኖሚያዊ እና በመሰረተ ልማት ዘርፎች እየተመዘገቡ የሚገኙ ስኬቶችን አጠናክሮ ለማስቀጠል ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ አቶ ጌቱ ማረጋገጣቸውን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review