AMN – ኅዳር 10/2017 ዓ.ም
የብልፅግና ፓርቲ የ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ዕቅድ አፈፃፀም ግምገማ በአሶሳ ከተማ እየተካሄደ ነው።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ፤ በመድረኩ ባለፉት 3 ወራት በፓርቲው የተከናወኑ ዋና ዋና ተግባራት በስፋት የሚገመገሙ መሆኑን ጠቁመዋል።
በመድረኩ በፓርቲ ደረጃ ላሉ አደረጃጀቶች የተሰጡ ሥልጠናዎች አጠቃላይ ሁኔታ ምን እንደሚመስልም የሚዳሰስ ይሆናል ነው ያሉት።
በመቀጠል ፓርቲው ያዘጋጀው የአመራር ልማት ረቂቅ ፖሊሲ ላይ ውይይት በማድረግ እንዲዳብር ይደረጋል ብለዋል።
ረቂቅ ፖሊሲው ጠንካራ ፓርቲ፣ ጠንካራ ሀገረ መንግስት ለመገንባት እና የአመራር ልማት ሥራን ስትራቴጂካዊና ተቋማዊ በሆነ መልኩ ለመምራት እንዲያስችል የተዘጋጀ ረቂቅ ፓሊሲ ነው ብለዋል።
በሶስተኛ ደረጃ የፓርቲ መደበኛ ተግባራት አፈፃፀም መመዘኛ ላይ በመወያየት የማዳበር ስራ የመድረኩ አካል ነው ብለዋል።
ከቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ በተገኙ ተሞክሮዎች ላይ ወይይት እንደሚደረግም ጠቁመዋል።
በመጨረሻም በፓርቲ አባላት ምልመላ፣ግንባታና ስንብት ረቂቅ መመሪያና የፖለቲካ ትንተና ረቂቅ መመሪያ ቀርቦ ውይይት ይደረጋል ብለዋል።
የግምገማ መድረኩ የፓርቲውን አፈፃፀም በጋራ በመገምገም ያለበትን ደረጃ ለመለየትና የቀጣይ የተግባራትን ስኬታማነት ወደ ላቀ ደረጃ ማድረስን ያለመ ስለመሆኑም ገልጸዋል።
በሂደት ጠንካራና ዘመናዊ የክትትልና ድጋፍ ሥርአት ለመዘርጋት የሚያስችሉ ሃሳቦች ላይ ሰፊ ውይይት የሚደረግ መሆኑንም አመላክተዋል።
በቀጣይም ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በልማት፣ በሰላም፣ ህግና ስርዓትን በማስከበር፣በዴሞክራዊያዊ ስርዓት ግንባታ እና ወሳኝ በሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ብሔራዊ መግባባትና የተረጋጋ የፖለቲካ ስርዓት ለመገንባት በሚያስችል መልኩ የትብብር ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
በመድረኩ የፓርቲው የ3 ወራት የስራ አፈጻጸም ሪፖርት፣ በተለያዩ ክልሎች ውጤት የተገኘባቸው የፓርቲ ስራዎች እና ተሞክሮዎች የሚታዩ መሆኑን ኢዜአ ዘግቧል።
በግምገማ መድረኩ የፓርቲውን ምክትል ፕሬዝዳንት ጨምሮ የክልሎችና የከተማ አስተዳደር የፓርቲው ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ኃላፊዎች ተገኝተዋል።