የብልፅግና ፓርቲ የ9ወራት የፓርቲ ስራዎች አፈፃፀምን የተቋሙ የዘርፍ ሀላፊዎች የክልል ቅርንጫፍ ፅ/ቤት ኃላፊዎች እና ሌሎች የፓርቲ ቅርንጫፍ ፅ/ቤት አመራሮች በተገኙበት በዛሬው እለት መገምገማቸውን በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ሃላፊና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አደም ፋራህ ገለጹ፡፡
አቶ አደም በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባጋሩት መልዕክት፤ በ2017 በጀት አመት የፓርቲ ሥራዎቻችን ብልፅግና በቁሳዊና ሰብዓዊ ሀብት አቅሙ የተጠናከረ፣ በዘመናዊ መረጃና በአሰራር ሥርዓቱ የደረጀ፣ የተደራጀ፣ የተዋሐደ፣ የተጽእኖ አቅሙ የዳበረና እንደ ሀገር የትርክት የበላይነትና ቅቡልነትን ያረጋገጠ ፓርቲ እንዲሆን ማስቻልን እንደ ዋና ዓላማ በመያዝ ስንሰራ ቆይተናል ብለዋል።
በዚሁ መሰረት በ3ኛ ሩብ አመት አፈፃፀምን ለጋራ ዓላማ እና ተልእኮ በእሳቤዎችን ላይ ፀንተን በመቆም በፓርቲ መደበኛ ስራዎች፣ በንቅናቄ ተግባራት፣ የፖለቲካ፣ የፀጥታ እና የልማት ስራዎችን በተቀናጀ መልኩ በመፈፀም ዘርፈ ብዙ ውጤቶችን ማስመዝገብ መቻሉን ነው የገለጹት።
በተለይም በአበይት ሀገራዊ አጀንዳዎች ላይ ከፓርቲው አመራር፣ አባላት እና ከልዩ ልዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ተከታታይነት ያላቸው ውይይቶችን በማድረግ በወሳኝ ሀገራዊ ጉዳዮች መግባባት ለመፍጠር ከተደረገው ጥረት ባሻገር ከመድረኮቹ የመፍትሄ ሀሳቦችን እና ገንቢ ግብዓቶችን በመቃረም ፓርቲው በተከተለው አቅጣጫ ስኬታማ ስራዎችን መስራት የተቻለባቸው እድሎች መፈጠራቸውን ገልጸዋል።

ተቋማዊ አቅማችንን ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስም ፓርቲያችንን በአሰራር ስርዓቶች በማጠናከር፣ አደረጃጀቶቻችንን ተልእኳቸውን በብቃት የመፈፀም አቅም በማጎልበት፣ ቀጣይነት ባለው መልኩ የአመራርና አባላት አቅም በመገንባት፣ የአመራር ምዘና እና የማስተካከያ የእርምት እርምጃዎችን በመውሰድ እና የአመራርና የአባላት የተግባር አፈፃፀም በማሻሻል ረገድ ተጨባጭ ስኬቶችን አስመዝግበናል ብለዋል።
ከዚህ በተጨማሪም የወጣት እና የሴት ክንፍ መዋቅሮችን በማጠናከር፣ በሀገር ውስጥ ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በትብብር በመስራት እንዲሁም ከውጭ እህት ፓርቲዎች ጋር መርህን በጠበቀ አኳኃን ብሄራዊ ጥቅሞችን እና ክብርን በሚያስጠብቅ መልኩ ለጋራ አላማ በጋራ በመስራት ረገድ የተሰሩ ስራዎች ፍሬያማ እንደነበሩ አብራርተዋል።
በአብይት ፓርቲያዊ ኩነቶች አፈፃፀም ላይም የብልፅግና ፓርቲ 2ኛ መደበኛ ጉባኤ በስኬት እንዲጠናቀቅ እና የፓርቲው 5ኛ አመት የምስረታ በዓል በሰብዓዊነት እና በሰው ተኮር እሳቤዎች ደምቆ እንዲከበር በማድረግ ተጨባጭ ፖለቲካዊ ውጤቶች መመዝገባቸውንም ነው የገለጹት።
በቀጣይም ቀሪ የበጀት አመቱን ሥራዎችን በተናበበ፣ በተቀናጀና በተሟላ መልኩ በጥራት መፈፀም፣ በየደረጃው የሚካሄዱ ውይይቶችና ግምገማዎች ችግር ፈቺ እንዲሆኑ ማድረግ፣ የአባላት የምልመላ ጥራት ማረጋገጥ፣ የፓርቲ አደጀጀቶች ተልዕኳቸውን በብቃት እንዲወጡ ማድረግ፣ የተግባር አፈፃፀም ውጤታማነት እና የሥነ ምግባር ችግር ያለባቸው አመራርና አባላት የማጥራት ሥራ መስራት እና ሁሉንም አማራጮች በመጠቀም ውጤታማ የሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ሥራዎች እንደሚሰሩም አረጋግጠዋል፡፡