AMN – ጥር 24/2017 ዓ.ም
የብሪክስ አባል ሀገራት (የሩሲያ እና የደቡብ አፍሪካ) እህት ፓርቲዎች ከብልጽግና ፓርቲ ጋር ያላቸውን ግንኙነት በማጠናከር በትብብር ለመስራት ያላቸውን ፍላጎት ገልጸዋል፡፡
‘ከቃል እስከ ባህል’ በሚል መሪ ሀሳብ እየተካሄደ በሚገኘው የብልጽግና ፓርቲ ሁለተኛ መደበኛ ጉባዔ የመክፈቻ ሥነ-ሥርዓት ላይ የብሪክስ አባል ሀገራት እህት ፓርቲ ተወካዮች መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
የዩናይትድ ሩሲያ ፓርቲ ሱፕሪም ካውንስል ቢሮ አባልና የሩስያ ፌዴሬሽን ሴናተር አንድሬ ክሊሞቭ እንዳሉት የኢትዮጵያና የሩሲያ የሁለትዮሽ ግንኙነት እና አጋርነት ይበልጥ ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡
ኢትዮጵያ እና ሩሲያ ዘመናትን የተሻገረ ወዳጅነት እና ትብብር እንዳላቸው ያወሱት ተወካዩ ይህ ባለብዙ ወገን እና በበርካታ መስኮች ላይ የተመሰረተው ግንኙነት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አውስተዋል፡፡
ይህ ጉባኤ የኢትዮጵያን መጻኢ ብልጽግና እንደሚያመላክት አስረድተው በዚህም ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረክ ያላትን ተደማጭነት እንደሚያሳድገው እምነታቸው መሆኑን አስረድተዋል።
የሁለቱ አገራት አጋርነት በተለይም በብሪክስ አባል አገራት አጋርነት መድረክ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል እና ለዚህም እንደሚሰራ አመልክተዋል፡፡
የዩናይትድ ሩሲያ ገዢ ፓርቲም ከብልጽግና ጋር ያለውን ግንኙነት የበለጠ በማጠናከር በትብብር እንደሚሰራ ጠቁመዋል፡፡
ለብልጽግና ፓርቲ ስኬት መልካም ምኞታቸውንም ገልጸዋል።
የደቡብ አፍሪካው ናሽናል ኮንግረንስ ፓርቲ ስራ አስፈፃሚ አባል ኑዶሎ ኪቤት በበኩላቸው ባስተላለፉት መልዕክት፣ ኢትዮጵያ ለአፍሪካ አንድነት መሰረት ከመጣል ጀምሮ ለአህጉሪቱ ሰላም እና እድገት መረጋገጥ የአንበሳውን ድርሻ እየተወጣች ነው ብለዋል፡፡
ለኢትዮጵያ እድገት እና ብልጽግና በትጋት እየሰሩ ላሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና አመራራቸው ትልቅ አድናቆት እንዳላቸውም አመልክተዋል፡፡
ኢትዮጵያ ለአፍሪካ አንድነት፤ ሰላም እና ልማት እየተጫወተችው ያለው ሚና ከፍተኛ መሆኑን የተናገሩት ተወካዩዋ ይህ ሚናዋ ዛሬም ተጠናክሮ መቀጠሉን አንስተዋል፡፡
ኢትዮጵያ ለአፍሪካ አንድነት እና ነፃነት ምሳሌ ከመሆኗ ባሻገር የጥንካሬዋ እና የጽናቷ አብነት መሆኗንም ገልጸዋል።
በቀጣይም የደቡብ አፍሪካ ናሽናል ኮንግረንስ ፓርቲ ከብልጽግና ፓርቲ ጋር በትብብር እንደሚሰራ አመላክተዋል፡፡
የአፍሪካን ልማት እና እድገት ለማረጋገጥ እንዲሁም ሰላሟን እና የዳበረ የዴሞክራሲ ስርአትን ለማጎልበት የጋራ ጥረታችን ተጠናክሮ ይቀጥላልም ብለዋል፡፡
ለአፍሪካ ሰላም እና እድገት መረጋገጥ አፍሪካውያን ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ተቀራርበው እና አንድ ሆነው መስራት እንዳለባቸውም አውስተዋል፡፡
በሰለሞን በቀለ