ነዋሪዎች በአውቶቡሱ መዘግየት ምክንያት መሄጃ ስለሌላቸው ጸሐይና ንፋስ እየተፈራረቀባቸው ቆመዋል፡፡ ህፃናት የያዙ እናቶች የልጆቻቸውን ፊት ከሚገርፈው ነፋስ ለማዳን ቢጥሩም መፍትሄ የለውምና በተስፋ መቁረጥ ስሜት የከተማ አውቶቡሱን መምጣት ሲጠባበቁ መመልከቱ የተለመደ ሆኖ ቀጥሏል። “የአውቶቡስ ፌርማታ ላይ ‘ወራጅ አለ!’፣ ‘ልጅ ይዘናል’፣ ‘አቅመ ደካማ ነን!’ የሚሉ ተሳፋሪዎች ድምፃቸው ጎልቶ ቢሰማም ሰምተው እንዳልሰሙ በፍጥነት ፌርማታውን አልፈው የሚሄዱ አንዳንድ የከተማ አውቶቡስ አሽከርካሪዎች ያጋጥመናል። በተለይ ጠዋት ከ4 ሰዓት እስከ 5 ሰዓት ባለው ጊዜ በሻይ እረፍት ስም የሚቆሙ አውቶቡሶች በመኖራቸው አሰልቺ የሆነ ረዥም ሰልፍ ለመሰለፍ እንገደዳለን፡፡ ጊዜያችንንም በመሰለፍ እናባክናለን። በዚህ ምክንያት የከተማ አውስቶቡስ ለመጠቀም እንግልት እያጋጠመን በመሆኑ መፍትሄ ይበጅልን” ብለዋል፤ ከሜክሲኮ ወደ ጀሞ አንድ ሲጓዙ የዝግጅት ክፍላችን በብዙሃን ትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ ያነጋገራቸው አቶ ምትኩ ኩመላ፡፡
መንግስት የከተማ አውቶቡስ ብዛትን በመጨመር ረገድ እያደረገ ያለው እንቅስቃሴ ይበል የሚያሰኝ ነው፡፡ ነገር ግን በአሁኑ ወቅት የትራንስፖርት ታሪፍ በመጨመሩ ምክንያት በርካታ ህብረተሰብ አውቶቡስ መጠቀምን ምርጫ እያደረገ ነው፡፡ በዚህም ተጨናንቆ የመሄዱ ጉዳይ ከወትሮው እየባሰ መጥቷል፡፡ ስለዚህ የከተማ አውቶቡስ ቁጥሩ አሁን ካለውም እንዲጨምር ቢደረግ ህብረተሰቡን የበለጠ ተጠቃሚ ለማድረግ ያስችላል ሲሉም አክለዋል፡፡
አቶ ታምሩ ለታም በዚሁ መስመር ሲጓዙ የዝግጅት ክፍላችን ያነጋገራቸው አስተያየት ሰጪ ናቸው፡፡ “የከተማ አውቶቡስ አገልግሎት ቀድሞ ከነበረው እየተሻሻለ ነው፡፡ ሜክሲኮ አካባቢ በፊት ተራ አስከባሪ ባለመኖሩ ለመሳፈር በጣም መጨናነቅና መገፋፋት ነበር፡፡ አሁን አስተባባሪዎች አሉ፡፡ በሰዓቱም ይገኛሉ፡፡ በመጣንበት አግባብ እንደቀድሞው ሳንጋፋ በስርዓት እንሳፈራለን፡፡ ይህ እንዳለ ሆኖ ግን አንዳንድ አሽከርካሪዎች በቀለበት መንገድ የሚሄዱ አሉ፡፡ ለመሻገር ስለሚያስቸግር ወደ ቀለበቱ ሳይገቡ መውረድ በሚቻልበት ቦታ ቢያወርዱና ቢያሳፍሩን ጥሩ ነው፡፡ የአውቶቡሶቹ ምልልስም ቢጨምር መልካም ነው” ብለዋል፡፡
ከሜክሲኮ ጀሞ አንድ የስምሪት መስመር ያገኘናቸው የከተማ አውቶቡስ ካፒቴን የሆኑት የሺሃረግ በላቸው ስለ አገልግሎት አሰጣጣቸው በተለይ ህዝቡ የሚያነሳው ፌርማታ ዘሎ መሄድ ጠይቀናቸው ነበር፡፡ “ህዝቡን ለማገልገል በተሰጠኝ ሃላፊነት እያገለገልኩ ነው፡፡ በየፌርማታው መጫንና ማውረድ ስላለብኝ ፌርማታ አልዘልም። ይህን ተግባር ሁሌም አከናውናለሁ” ብለዋል፡፡
ካፒቴን የሺሃረግ በአስተያየታቸው፣ አውቶቡሱ ከአቅም በላይ ሞልቶ ካልሆነና ሌላ ችግር ከሌለበት ፌርማታ አልፎ መሄድ ተገቢ አይደለም። ከዚህ ባለፈ አንዳንድ ተሳፋሪዎች ሳይከፍሉ ገብተው “ክፈሉ” ሲባሉ አላስፈላጊ ቃላት የሚናገሩ አሉ። የህዝብ አገልጋይ እስከሆን ድረስ ሊያከብሩን ይገባል። እኛ አሽከርካሪዎችም በምንችለው አቅም ህዝቡን አክብረን በተገቢው መንገድ ፌርማታ ሳናልፍ ማገልገል ይኖርብናል ሲሉ ገልፀዋል፡፡
የጋዜጣው ዝግጅት ክፍል ቅኝት ባደረገበት ወቅት ከሜክሲኮ ወደ ጀሞ አንድ መስመር የተወሰኑ የሚጭኑ አውቶቡሶች ቢኖሩም በርካታ የተሰለፉ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተመልክቷል፡፡
ሌላው ቅኝት ያደረግንበት የአውቶቡስ መሳፍሪያና ማውረጃ ማዕከል መገናኛ አካባቢ ነው። አቶ መልካምሰው ውብሸት ከመገናኛ ወደ ቂሊንጦ ለመጓዝ ተሰልፈው የከተማ አውቶቡስ እየተጠባበቁ ነው ያገኘናቸው፡፡ “የከተማ አውቶቡስ አገልግሎቱ እየተሻሻለ መጥቷል፡፡ ሆኖም በዚህ መስመር ከመገናኛ ወደ ቂሊንጦ አውቶቡስ አግኝቶ ለመሄድ ቀላል ቢሆንም ከቂሊንጦ ወደ መገናኛ ለመመለስ ግን በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡ ብዙ ጊዜ አውቶቡሱ በሰዓቱ አይመጣም። ምልልሱ ትንሽ በመሆኑ ታክሲ እንድንጠቀም እየተገደድን ነው። ቶሎ ቶሎ ቢመጣልን ጊዜያችንን በአግባቡ እንድንጠቀም ይረዳናል” ብለዋል።
ወጣት ቅድስት ዓለምእሸትንም ከመገናኛ- ኮዬ ፈቼ መስመር የከተማ አውቶቡስ ለመሳፈር ተሰልፋ ነው ያገኘናት፡፡ በዚህ መስመር አውቶቡስ መጠቀም ከጀመርኩ ሦስት ሳምንት ሆኖኛል። የበፊቱን ችግር ባላውቅም መጠቀም ከጀመርኩ በኋላ ጠዋት 12፡30 ስወጣ አንበሳም ሸገር አውቶቡስም አገኛለሁ፡፡ በየፌርማታውም ያቆማሉ። ስመለስ ተሰልፌም ቢሆን አገኛለሁ፡፡ ምንም ችግር አልገጠመኝም፡፡ አገልግሎቱ በዚሁ ይቀጥል ስትል ሃሳቧን አቅርባለች፡፡
የከተማ አውቶቡስ ካፒቴን ብሩክ ገበየሁ ስምሪታቸው ከመገናኛ ኮዬ ፈጨ መስመር ነው። ስለ አገልግሎታቸው ጠይቀናቸው ሲመልሱ፤ “ህዝቡን ለማገልገል ባለኝ አቅም እየሰራሁ ነው። ምን አልባት መገናኛ አካባቢ ባለው የመንገድ መሰራት ምክንያት የሥራ መግቢያና መውጪያ ሰዓት የመንገድ መጨናነቅ ቢኖርም በስራ ቦታዬ ሰዓቴን ጠብቄ ነው የማገለግለው፡፡ ፌርማታ አልዘልም፡፡ አልፎ አልፎ ከመጠን በላይ ከሞላ ቦታ ስለማይኖርና ለአውቶቡሱም ደህንነት ሲባል መሙላቱን በእጄ ምልክት ሰጥቼ ነው የማልፈው” ብለዋል፡፡
አንዳንዴ ሀሳብ ውስጥ ሆነው የሚወርዱበትን ፌርማታ የሚረሱና ያለፌርማታ አውርዱን የሚሉ ተጠቃሚዎች ያጋጥማሉ፡፡ ይህንንም የአሽከርካሪው ችግር የሚያደርጉ አሉ። ከዚህ ውጪ እያወቁ በተለይ ሳይሞሉ ፌርማታ የሚዘልሉ አሽከርካሪዎች ካሉ ግን አግባብነት የለውም፡፡ ህሊናችንም ሊወቅሰን ይገባል ይላሉ ካፒቴን ብሩክ፡፡
እኛም በአካባቢው ባደረግነው ቅኝት መገናኛ የእግረኛ የውስጥ ለውስጥ መንገድ ግንባታ እየተካሄደ በመሆኑ በመንገድ መጨናነቁ ምክንያት አብዛኛው የከተማ አውቶቡሶቹ ተሳፋሪ ጭነው ለመሄድ ቆመው ተመልክተናል፡፡ ሌሎች ተሳፋሪዎችም ሰልፍ ይዘው የአውቶቡስ መምጣትን ሲጠባበቁ ታዝበናል፡፡
አገልግሎት ሰጪው ተቋም ምን ይላል?
የዝግጅት ክፍላችን ከከተማ አውቶቡስ አገልግሎት አሰጣጥ ጋር ተያይዞ ከትራንስፖርት ተጠቃሚዎች ያገኘውን መረጃ መሰረት በማድረግ ምላሽ እንዲሰጡን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የከተማ አውቶቡስ አገልግሎት ድርጅት ዋና ዳይሬክተር አቶ አካሉ አሰፋን አነጋግሯል፡፡ ዋና ዳይሬከተሩ እንደገለፁት፣ በመዲናዋ ለረዥም ዓመታት በውስን አውቶቡሶች ለህብረተሰቡ የትራንስፖርት አገልግሎት ሲሰጥ ቆይቷል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከተማ አስተዳደሩ የከተማዋን እድገት እንዲሁም የህዝቡን የአውቶቡስ ተጠቃሚነት ፍላጎትና ቁጥር መጨመር ታሳቢ በማድረግ አገልግሎቱን ለማሻሻል የተለያዩ ተግባራትን ሲያከናውን ቆይቷል፡፡ ከ2010 ዓ.ም በኋላም አንበሳና ሸገር አውቶቡሶች ከተናጠል ይልቅ አንድ ላይ እንዲሆኑ በማድረግ እና ተጨማሪ 1 ሺህ አውቶቡስ በመግዛት አገልግሎቱ ለህብረተሰቡ እየተሰጠ ይገኛል፡፡ አንበሳና ሸገር አውቶቡሶች ከተቀላቀሉ በኋላ ከዚህ ቀደም በአስተዳደር ዘርፍ፣ በጥገና ሂደት፣ በዲፖ አጠቃቀም የነበሩ ችግሮችን መፍታት ተችሏል፡፡
ያነጋገርናቸው የከተማ አውቶቡስ ተጠቃሚዎች በአብዛኛው ፌርማታ አልፎ የመሄድና የአውቶቡስ ምልልሱ አነስተኛ መሆን አስመልክቶ ላነሱት ቅሬታ ዋና ዳይሬክተሩ ምላሽ ሲሰጡ፤ “የህብረተሰቡ የከተማ አውቶቡስ የመጠቀም ፍላጎት እያደገ መጥቷል፡፡ ነገር ግን የህዝቡ ቁጥር ከመጨመር ጋር ተያይዞ ፍላጎትና የአገልግሎት ተደራሽቱ ተመጣጣኝ አይደለም፡፡ አገልግሎት የሚሰጠው ባለው ውስን ሀብት በመሆኑ አቅርቦትና ፍላጎቱ ባለመጣጣሙ ከህብረተሰቡ ቅሬታዎች በየጊዜው እንደሚነሱ ይታወቃል። ይህም አውቶቡሶች በቶሎ አይደርሱም፣ ቆመን ውለናል የሚሉና ሌሎች ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር የተገናኙ ጉዳዮችን ያነሳሉ” ብለዋል፡፡
ፌርማታ በተለያዩ ምክንያቶች ሊዘለል ይችላል፡፡ አንደኛው ያለው የአውቶቡስ ተጠቃሚና አቅርቦቱ የተጣጣመ ስላልሆነ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የህብረተሰብ ክፍል የሚሳፈር በመሆኑ ከሞላ ሊዘለል ይችላል፡፡ ሁለተኛው ሰርቪስ የሚሰጥ አውቶቡስ ከሆነ ያልፋል ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ተገቢ ባልሆነ ሁኔታ ፌርማታ ላይ ቆመው መጫን ሲገባቸው የሚዘሉ አልፎ አልፎ እንዳሉ አልሸሸጉም፡፡ ይህን ለማስተካከል በአሁኑ ወቅት በቴክኖሎጂ ቁጥጥር ተጀምሯል። ከዚህ በኋላ አልፈው የሚሄዱ ከተገኙ የቃል፣ የፅሁፍና ከስራ እስከማባረር የሚደርስ እርምጃ እንደሚወሰድ ዋና ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል፡፡
ከሻይ ሰዓት ጋር ተያይዞ ለተነሳው ጥያቄ አቶ አካሉ ሲመልሱ፤ የከተማ አውቶቡስ ካፒቴኖች፣ ቲኬት ቆራጮች፣ የሥምሪትና ሌሎችም ባለሙያዎች ህብረተሰቡን ለማገልገል ከከተማዋ ጫፍ ቦታዎች፣ ከከተማዋ ዙሪያ ከቢሾፍቱ፣ ከለገጣፎ እንዲሁም ከ67 ኪሎ ሜትር ጭምር ለስራ የሚወጡት ከለሊቱ 10፡30 ሰዓት ጀምሮ ነው፡፡ አሽከርካሪዎችም ቁርስ ሳይበሉ ስምሪት ይጀምራሉ፡፡ በቀን ከ15 እስከ 30 ደቂቃ የሻይ እረፍት አላቸው፡፡ ከቀን በተጨማሪ እስከ ምሽትም ነው የሚሰሩት፡፡ አገልግሎቱ በከፍተኛ ድካምና ትጋት የሚሰጥ በመሆኑ ህዝቡ አልፎ አልፎ ሰዓቱን ቢያሳልፉ እንዲረዳቸውና ችግሩ የባሰ ከሆነ ደግሞ ማሳወቅ እንዳለበት ገልፀዋል፡፡
አቶ አካሉ እንዳብራሩት፤ በከተማ አውቶቡስ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ከህዝቡ የሚነሱ የተለያዩ ቅሬታዎችንና ለሚታዩ ችግሮች መፍትሄ ለመስጠት ከተማ አስተዳደሩ ድርጅቱ ተቋማዊ ሪፎርም እንዲሰራ ወስኗል፡፡ በአሁኑ ወቅትም በድርጅቱ የሪፎርም ስራው ተጀምሮ ወደ መጠናቀቁ ተቃርቧል። ሪፎርሙ ሦስት መሰረታዊ ጉዳዮች ላይ በማተኮር ነው እየተሰራ ያለው። ይህም ከአደረጃጀት፣ ከቴክኖሎጂ እንዲሁም ከአሰራር፣ መመሪያና ህጎች ጋር ያሉ ችግሮችን መፍታትን ያለመ ነው፡፡ በዓለም ላይ ማንኛውም የህዝብ ትራንስፖርት ቴክኖሎጂ የሚጠቀም ነው። ስለዚህ በሪፎርሙ ዋናው ትኩረት የሚሰጠው ቀድሞ ያልነበረውን አገልግሎቱን በቴክኖሎጂ ማዘመን፣ የክፍያ ስርዓቱ ከወረቀት ቲኬት ይልቅ በኤሌክትሮኒክስ የክፍያ ስርዓት ማድረግ፣ ስምሪቱም ቁጥጥሩም ሙሉ በሙሉ በቴክኖሎጂ የተደገፈ እንዲሆን በከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ ሀብት ፈስሶበት በርካታ ስራዎች እየተሰሩ ነው፡፡
በአሁኑ ወቅትም የሪፎርሙ አንድ አካል የሆነውን የቁጥጥር ስርዓቱን በቴክኖሎጂ የመደገፍ ስራ ሙከራ መጀመሩን ዋና ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል። አንድ አውቶቡስ ከ20 ደቂቃ በላይ መቆም አይችልም፡፡ ከተመደበበት መስመር ውጪም መቆም አይችልም፡፡ ከዚህ ቀደም እንደነበረው እንደፈለጉ ማንኛውም ቦታ በማቆም ጊዜን ማባከን አሁን አይቻልም፡፡ በአምስቱም የአውቶቡስ ዲፖዎች ቴክኖሎጂዎች ተገጥመዋል። በአውቶቡስ ውስጥ ያሉ እቅስቃሴዎችን ጭምር በቴክኖሎጂ ቁጥጥር ይደረጋል፡፡
እያንዳንዱ ዲፖ የትኛው አውቶቡስ የት እንደቆመ፣ ስንት ደቂቃ እየተጓዘ እንደሆነ፣ ፌርማታ እየዘለለ መሆኑንም ጭምር ቁጥጥር ያደርጋል፡፡ በከተማ አውቶቡስ አሽከርካሪዎች የሥነ ምግባር ችግሮች፣ በአውቶቡስ ዲፖዎች የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮች ካሉ ለመቆጣጠር እንዲያስችልም በሁሉም ዲፖዎች የደህንነት ካሜራ (ሲሲቲቪ) ተገጥሟል፡፡
በሌላ በኩል የክፍያ ስርዓቱን ለማዘመን እየተሰራ ነው፡፡ ጊዜና ከፍተኛ ሀብት የሚፈልግ በመሆኑ ይህን ለማስተካከል የከተማ አስተዳደሩ በቴክኖሎጂ ለማስደገፍ ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ነው፡፡ ሙሉ በሙሉ ሪፎርሙ ከተጠናቀቀ በኋላ በህብረተሰቡ የሚነሱ የአገልግሎት አሰጣጥ ቅሬታዎች ለመፍታት፣ የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን ለማሳደግ፣ የአሰራር ጉድለትና የሥነ ምግባር ችግሮችንም ለማረም ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረውም ነው ዋና ዳይሬክተሩ የጠቁሙት፡፡
እንደ አቶ አካሉ ገለፃ፤ ድርጅቱ የተሽከርካሪ፣ የካፒቴንና የቲኬት ቆራጭ እጥረት ያለበት ሲሆን እነዚህን ተግዳሮቶች በመቋቋም ከሰራተኞቹ ጋር በመሆን ለህብረተሰቡ ተገቢ የሆነ የከተማ አውቶቡስ አገልግሎት ለመስጠት ቀን ከሌት እየሠራ ነው። ከዚህ አልፎ ከተማ አስተዳደሩና ትራንስፖርት ቢሮም ጭምር በጋራ በመስራት በተቋሙ ያሉ እጥረቶችን ለመሙላትና አገልግሎቱን የተሳለጠ ለማድረግ ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገ ነው፡፡
ህብረተሰቡ ሊያግዘን የሚገባው ተግባር አለ የሚሉት አቶ አካሉ፣ በአገልግሎቱ ላይ የሚያጋጥም ችግርና ብልሹ አሰራር ሲመለከት በ8991 ጥቆማ ሊያደርግ ይገባል፡፡ ያለን ሃብት ውስን በመሆኑም ህብረተሰቡ አውቶቡሶችን በአግባቡ ሊጠቀም ይገባል። መቀመጫ ከሌለ ቆመን አንሄድም የሚሉ አሉ፡፡ በዓለም ላይ ባደጉት ሃገራትም ጭምር የህዝብ ትራንስፖርት ላይ ቆሜ አልሄድም አይባልም። አውቶቡስ ከተማ ውስጥ ቢበዛ 30 ደቂቃ ይጓዛል፡፡ ስለዚህ ህብረተሰቡ ደርሶ እስኪመለስ 1 ሰዓት ከመቆም ይልቅ 30 ደቂቃ ቆሞ በመሄድ ወደሚፈልገው ቦታ መድረስ ስለሚችል አገልግሎቱን በተገቢው እንዲጠቀም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ገለፃ፣ ከተማ አስተዳደሩ ባለው አቅም ችግሩን ለመፍታት በተለያዩ ጊዜያት ትኩረት አድርጎ እየሰራ ነው፡፡ እስከ 2010 ዓ.ም ድረስ ከ460 የማይበልጡ የከተማ አውቶቡሶች የነበሩ ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት ከ1 ሺህ 400 በላይ አውቶቡሶች በማድረስ አስተዳደሩ ህዝቡን ተጠቃሚ ለማድረግና የህዝቡን ጥያቄ ለመፍታት እየሠራ ነው።
በአሁኑ ወቅት ድርጅቱ 7 ሺህ 262 ሰራተኞች ይዞ እየሠራ ሲሆን በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች በ177 የስምሪት መስመሮች የከተማ አውቶቡስ አገልግሎቱ እየተሰጠ ይገኛል፡፡ በቀጣይም እየተነሱ ያሉ ቅሬታዎችን በሪፎርሙ አማካኝነት በአጭር ጊዜ ለመፍታትና ለህብረተሰቡ ተገቢ የሆነ የከተማ አውቶቡስ አገልግሎት ለመስጠት በከተማ አስተዳደሩ፣ በትራንስፖት ቢሮ፣ በተቋሙ አመራሮችና በባለሙያዎች በተጠናከረ መልኩ እየተሰራ መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል፡፡
እኛም የብዙሃን ትራንስፖርት አገልግሎቱን በማሳለጥ ረገድ የሚኖረው አስተዋጽኦ አይተኬ ነው። ይህን ታሳቢ ባደረገ መልኩ የሚስተዋሉ ችግሮችን በመቅረፍ አገልግሎት አሰጣጡን ማሳደግ ይገባል መልዕክታችን ነው፡፡
በሰገነት አስማማው