AMN – መጋቢት 16/2017 ዓ/ም
የቬንዙዌላን የነዳጅ ዘይት የሚገዛ የትኛውም ሀገር የ25 በመቶ ታሪፍ ይጣልበታል ሲሉ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስጠነቀቁ።
“ቬንዙዌላ ለአሜሪካ እና ለምናጋራው ነፃነት በጣም ጠላት የሆነች ሀገር ናት ብለዋል፡፡
ስለሆነም ማንኛውም የነዳጅ ዘይት እና ጋዝ ከቬንዙዌላ የሚገዛ ሀገር ከአሜሪካ ጋር በሚኖረው የንግድ ልውውጥ የ25 በመቶ ታሪፍ ለመክፈል ይገደዳል” ሲሉ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ባሰፈሩት መልዕክት አስታውቀዋል።
ቬንዙዌላ ያለምንም ማስረጃ እንደ ትሬን ዴ አራጉዋ ያሉ ወንጀለኞችን ሆን ብላ ወደ አሜሪካ ትልካለች ሲሉም ትራምፕ ወንጅለዋል።
ዜናው ይፋ የሆነው ፕሬዚዳንቱ ቀደም ብለው ወደ ሀገር ውስጥ በሚገቡ የመድኃኒት፣ የተሸከርካሪ እና የእንጨት ምርቶች ላይ ለመጣል ያሰቡትን የ25 በመቶ የታሪፍ ጭማሪ እንደሚያዘገዩ ካስታወቁ በኋላ ነው፡፡
ቬንዙዌላ ባለፈው ዓመት ለአሜሪካ ከፍተኛ የነዳጅ ዘይት አቅራቢ ከሆኑ ሀገራት አንዷ እንደነበረች የአሜሪካ የንግድ ክፍል መረጃ ያመላክታል።
አሜሪካ በፈረንጆቹ 2024 በአጠቃላይ 5.6 ቢሊየን ዶላር የሚያወጣ የነዳጅ ዘይት እና ጋዝ መግዛቷን ሲኤንኤን ዘግቧል።
ይህም የመጣው የባይደን አስተዳደር በፈረንጆቹ 2023 በቬንዙዌላ የነዳጅ ዘይት ላይ ተጥሎ የነበረውን ማዕቀብ ለአጭር ጊዜ ካነሳ በኋላ ነበር፡፡
ነገር ግን የባይደን አስተዳደር የሀገሪቱን መሪ ኒኮላስ ማዱሮ ነፃ እና ፍትሃዊ ምርጫ አላካሄዱም በሚል በሚያዝያ ወር 2024 ማዕቀቡ ወደነበረበት ተመልሷል።
ነገር ግን ቼቭሮን ተሰኘው የተፈቀደለት የነዳጅ አውጪ ሸሪክ በሀገሪቱ ውስጥ በመኖሩ የቬንዙዌላ የነዳጅ ዘይት ወደ አሜሪካ መግባቱን ቀጥሏል፡፡
ይሁንና ፈቃዱ በቀጣዩ የፈረንጆቹ ሚያዝያ 3 ቀን 2025 ሊሰረዝ የነበረ ቢሆንም፣ ትራምፕ ባለፈው ሳምንት ከቼቭሮን ዋና ስራ አስፈፃሚ ማይክ ዊርዝ እና ሌሎች የኩባንያው ሥራ አስፈፃሚዎች ጋር በተደረገ ውይይት እስከ ግንቦት ወር ድረስ እንዲራዘም ተደርጓል።
ቀድሞም የፈቃዱ መሰረዝ ሀሳብ የመጣው፣ ቬንዙዌላ በትራምፕ አስተዳደር ወንጀለኞች በሚል ከአሜሪካ የተባረሩ ስደተኞችን ለመቀበል ፈቃደኛ ባለመሆኗ እንደ ቅጣት አይነት ለማቅረብ ነበር፡፡
በኋላም ቬንዙዌላ 200 ስደተኞችን ከአሜሪካ ወደ ሀገሯ ለመመለስ በረራዎች እንዲቀጥሉ ከስምምነት ላይ ደርሳለች።
ይሁን እንጂ አንዳንድ የተባረሩ ዜጎች ዘመዶች ቤተሰቦቻቸው ምንም አይነት የወንጀል ድርጊት ውስጥ እንዳልነበሩ ለሲኤንኤን ተናግረዋል፡፡
በወርቅነህ አቢዮ