የተለየዩ ሀገራት መሪዎች በሮማው ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ፖፕ ፍራንሲስ ህልፈት የተሰማቸውን ሃዘን እየገለጹ ነው፡፡
የሮማ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ፖፕ ፍራንሲስ በ88 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም ድካም ማረፋቸውን ቫቲካን ይፋ ማድረጓ ይታወቃል፡፡
ይህንን ተከትሎም የተለያዩ የዓለም ሀገራት መሪዎች ሀዘናቸውን እየገለጹ ነው፡፡
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ባሰፈሩት መልዕክት፣ በካቶሊካዊት ቤተ-ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ፖፕ ፍራንሲስ ህልፈተ ህይወት የተሰማቸውን ሀዘን ገልጸዋል፡፡
ርህራሄ፣ ትህትናቸው እና ለሰው ልጆች የነበራቸው የአገልግሎት ትሩፋትም በትውልዶች ይቀጥላል ሲሉም አስፍረዋል።
የኬንያው ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ የጳጳሱን ማለፍ ለክርስትያኑ አለም “ትልቅ ጉዳት” በማለት የገለጹ ሲሆን ሁለንተናዊ ፍትህን ለማስፈን ቁርጠኛ ነበሩ” በማለት አወድሰዋቸዋል።
ዋይት ሀውስ በይፋዊ ገጹ ባሰፈረው የሀዘን መግለጫ፤ “ሊቀ ጳጳስ ፖፕ ፍራንሲስ ነፍሳቸው በሠላም ትረፍ” በማለት ገልጿል።
በተመሳሳይ ክሬምሊን ባወጣው የሀዘን መግለጫ፤ የሩሲያው ፕሬዚደንት ቭላድሚር ፑቲን ሊቀ ጳጳስ ፖፕ ፍራንሲስ “የሰብዓዊነት እና የፍትህ ጠበቃ” ነበሩ በማለት መግለጻቸውን አስታውቋል።
የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎዛ ፤ ፖፕ ፍራንሲስ ትህትናን ለማስተማር እና ቤተክርስቲያንን እና ዓለምን የተሻለ ለማድረግ ቁርጠኛ እንደነበሩ በማንሳት ሀዘናቸውን ገልጸዋል፡፡
በተመሳሳይ የአውስትራሊያው ጠቅላይ ሚኒስትር አንቶኒ አልባኔዝ ፤ፖፕ ፍራንሲስን “ዘመናዊ” በማለት የገለጿቸው ሲሆን ለአውስትራሊያ ካቶሊካውያን “ታማኝ አባት” ነበሩ ብለዋል፡፡
የናይጀሪያው ፕሬዚዳንት ቦላ ቲኑቡ ሊቀ ጳጳስ ፖፕ ፍራንሲስን “ለአየር ንብረት እንቅስቃሴ ድምጽ ነበሩ” ሲሉ አወድሰዋቸዋል፡፡
የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በኤክስ ገጻቸው ባሰፈሩት ፅሁፍ ፤ ሊቀ ጳጳስ ፖፕ ፍራንሲስ ፤ ቤተክርስቲያን ለድሆች ደስታና ተስፋ እንድታመጣ ሲያገለግሉ ነበር ብለዋል። ሰዎች እርስ በእርሳቸው እና ከተፈጥሮ ጋር እንዲስማሙ ጥረት ሲያደርጉ እንደነበር በመግለጽ በህልፈታቸው የተሰማቸውን ሀዘን ገልጸዋል፡፡
የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ኪር ስታርመር በኤክስ ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት፤ ፖፕ ፍራንሲስ “ለድሆች፣ ለተጨቆኑ እና ለተረሱ ሰዎች የቆሙ” ነበሩ ብለዋል።