ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት ቆይታ እስካሁን የተመዘገቡ ስኬቶችን ለአራት እና አምስት አመታት ደጋግመን ማምጣት ከቻልን የኢትዮጵያ ከፍታ እውን ይሆናል ሲሉ ተናግረዋል።
ባለፉት ሰባት ዓመታት የኢትዮጵያ መንግስት ለደመወዝ በየዓመቱ የሚያወጣው ገንዘብ በአማካይ 21 በመቶ ይጨምራል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ነገር ግን ይህ ወጪ እያንዳንዱ ሠራተኛ ጋር አይደርስም ብለዋል፡፡
የዚህ መሠረታዊ ምክንያትም ደግሞ በሰባት ዓመታት ውስጥ የመንግስት ሠራተኛው ቁጥር 44 በመቶ በመጨመሩ ነው፡፡
ከለውጡ በፊት አንድ ነጥብ 7 ሚሊየን የነበረው የመንግስት ሰራተኛው ቁጥር አሁን ላይ 2 ነጥብ 5 ሚሊየን መብለጡን አስታውቀዋል፡፡
በስድስት ዓመታት ውስጥ የመምህራን ቁጥር ብቻ በ36 በመቶ ጨምሯል፡፡ በዘርፉ የነበረውን የትምህርት ስብራት ለማሻሻል የተደረገ መሆኑንም በማከል፡፡
በአሁኑ ሰዓት በኢትዮጵያ ከ35 ሺ በላይ መዋለ ህፃናት ተገንብተዋል፡፡ ህፃናት ቀደም ሲል ወደ መደበኛ ትምህርት ቤት ሲገቡ የሚጋጥማቸው የሥነ ልቦና ችግር እንደማይኖርም አስገንዝበዋል፡፡
በጤናው ዘርፍ ደግሞ 53 በመቶ የጤና ባለሙያ ተጨምሯል፡፡
ዘንድሮ ለደመወዝ ጭማሪ 91 ቢሊየን ብር ነው የተበጀተው፣ ይህም እጅግ ዝቅተኛ ተከፋዮችን ታሳቢ በማድረግ እንደነበር ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ይህ ሲሆን ግን ሀገር ብዙ ነገር ቀንሳ እንጂ ተርፏት ያደረገችው አለመሆኑን አብራርተዋል፡፡
ብሔራዊ ጥቅም የሚመዘነው በግለሰብ ጥቅም ሳይሆን በጋራ ጥቅም መሆኑንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው አፅንኦት ሰጥተዋል፡፡
እያደግን ነው ዋጋ ግሽበትን ለመግራት እየሠራን ያለነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ኢትዮጵያ ውስጥ ዕድገት ሳይሆን ተዓምር ነው ያለው ብለዋል፡፡ ዕድገቱም ካሰብነው ለውጥ እና ጥራት በላይ እየተመዘገበ መሆኑን በማከል፡፡
ለአብነትም የያዝነው የማንሰራራት ዓመት የተመዘገቡ ስኬቶችን ለአራት እና አምስት አመታት ደጋግመን ማምጣት ከቻልን የኢትዮጵያ ከፍታ እውን ይሆናል ፤ ለዚህም የጋራ ጥረት ያስፈልጋል ሲሉ ገልጸዋል፡፡