“ይላል ዶጁ ፏ … ፏ … ይላል ዶጁ፣
ደስ የሚለኝ ሾፌር መልከ መልካም ልጁ፣
እኔስ አላውቀውም ይብላኝ ለወዳጁ፡፡
ፏ … ፏ … ይላል ዶጁ፤
ፈገግታውን ጋብዞ አንዴ ቢያናግረኝ፣
ይሄም አለ ለካ መውደዱ ጀመረኝ፡፡
ልክ እንደመኪናው እያሽከረከረ፣
ሹፌር ነው የኔ ፍቅር ልቤን ያበረረ “ ትላለች፣ ድምፃዊት ነፃነት መለሰ፡፡ እኛ ግን ስለሹፌሩ ሳይሆን ስለመኪና ለአፍታ ያህል እንጨዋወታለን፡፡ ™ፏ ፏ ይላል ዶጁ∫ ስለተዘፈነላት የላንቲካ መኪና ብቻ አይደለም፣ ስለሁሉም እንጅ፡፡ ደግሞም የወጋችን ጭብጥ ስለመኪናዎቹ ስሪት፣ ጉልበት እና ውበት ሳይሆን ሹፌሩም ተሽከርካሪውም አረፍ፣ ስለሚሉባቸው የመኪና ማቆሚያ ስፍራዎች ነው፡፡
በዓለም ትልቁ የመኪና ማቆሚያ በኤድመንተን ካናዳ የሚገኘው ዌስት ኤድመንተን ሞል ፓርኪንግ ሲሆን 20ሺህ ተሽከርካሪዎችን የመያዝ አቅም አለው። ይህ የመኪና ማቆሚያ ስፍራ የዌስት ኤድመንተን የገበያ እና የመዝናኛ ማዕከል እንደሆነም ይነገራል፡፡ የመኪና ማቆሚያ ቦታው በጣም ሰፊ ከመሆኑ የተነሳ 10 ሺህ ተጨማሪ መኪናዎችን ማሳረፊያ ስፍራም አለው፡፡ ይህ የመኪና ማቆሚያ ስፍራ እ.ኤ.አ ከ1981 ጀምሮ በዓለም አቀፉ የድንቃድንቅ መዝገብ ሰፍሮ ይገኛል፡፡
በ 19ኛው እና በ 20ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ የመኪና ምርቶች እየተስፋፉ መምጣታቸውን ተከትሎ የመኪና ማቆሚያ ቦታ አስፈላጊነት ግድ እየሆነ መጣ፡፡
እ.ኤ.አ. በ1905 ፓሪስ የመጀመሪያውን አውቶሜትድ የመኪና ማቆሚያ ስርዓት በጋራዥ ሩ ዴ ፖንቲዩ ውስጥ አስተዋወቀች፣ ተሽከርካሪዎችን ወደ ላይኛው ደረጃ ለማጓጓዝ የመኪና አሳንሰርን በመጠቀምም ፓሪስ፣ ለዘመናዊ አውቶማቲክ የመኪና ማቆሚያ ስርዓቶች ፈር ቀዳጅ ሆነች ይላል ሀርዲናግ አውቶ ፓርክ ሲስተምስ (Harding Autopark Systems) በ2021 ይፋ ያደረገው መረጃ፡፡
እነ ላስ ቬጋስን የመሳሰሉ የዓለማችን ከተሞች ላይ መኪና እየበዛ፣ ለተሽከርካሪና ለሰዎች የተሰሩ መንገዶች ለመኪና ማቆሚያነት እየዋሉ የሰዎች እንቅስቃሴ ሲገታና ውበታቸው ሲደበዝዝ ከተሞች በ 20ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ ላይ ስለመኪና ማቆሚያ፣ ስለጋራጆችና መሰል ስፍራዎች መጨነቅ ጀመሩ፡፡ ይላል በሮበርት ቬንቱሪ እና በዴኒዝ ስኮት ብራውን እ.ኤ.አ በ1972 የታተመው ከላስ ቬጋስ እንማር(Learning from Las Vegas) የተሰኘው መጽሐፍ፡፡
በዚህ መፅሐፍ ላይ እንደተገለፀው የመኪና ማቆሚያ ስፍራ ፋይዳው መኪናዎችን ከማቆም ይሻገራል። በመሆኑም ከተሞች ለመኪና ፓርኪንግ የሚጠቀሙባቸውን ሕንፃዎች ለገበያ ማዕከላት እና መሰል አገልግሎት መስጫ ተቋማት ጭምር እንዲያገለግሉና ለከተሞች ውበትም፣ የኢኮኖሚ ጉልበትም ለማህበረሰባዊ እንቅስቃሴ ጤናማ ረፍትም ይሆኑ ዘንድ ዘመናዊ መኪና ፓርኮቻቸውን የበለጠ ይጠቀሙባቸዋል፡፡
ከተሞች ባለንበት ዘመን የተራቀቁ ቴክኖሎጂዎችን በፓርኪንግ አገልግሎት መስጫዎች እየተጠቀሙ እንደሆነ ከላይ በጠቀስነው መፅሐፍ ሰፍሯል። ለአብነትም በጀርመን የሚገኘው ቮልስዋገን ተርሚናል፣ ተሽከርካሪዎችን ለማቆም ሮቦቶችን ይጠቀማል፡፡ ይህም ያሉ ክፍት ቦታዎችን በአግባቡ ለመጠቀምና ከዘመናዊ ካሜራዎች ባሻገር የንብረቶችን ደህንነት የበለጠ ለመጠበቅ እንደሚረዳቸውም ተመላክቷል፡፡
የዘመናዊ የመኪና ማቆሚያዎች፣ በቴክኖሎጂ፣ በሥነ ሕንፃ እና በከተማ ልማት ውስጥ ሰፊ ድርሻ አላቸው፡፡ የመኪናዎች ማቆሚያ ስፍራ ከከተሞች ዕድገትና ከሰው ልጅ ስልጣኔ ጋር ከፍ እያለ መምጣቱም በመፅሐፉ ተመላክቷል፡፡
እንደ መፅሐፉ ከሆነ ዘመናዊና ቀልጣፋ የተሽከርካሪ ማቆሚያ (ተርሚናል) ለከተማ ውበት፣ የሰውና ተሽከርካሪ መጨናነቅን ለመቀነስ፣ የአካባቢን ብክለትም ሆነ ሁለንተናዊ ጥራትን ለማሻሻል ወሳኝ ድርሻ አለው፡፡
በዓለም ዙሪያ ያሉ በርካታ ከተሞች የትራፊክ ፍሰቱን ምቹና ሰላማዊ ከማድረግ ባሻገር ለኢኮኖሚያዊ እና ለአካባቢ ጥበቃ ፋይዳ ያላቸው አዳዲስ የመኪና ማቆሚያ ግንባታዎችን ተግባራዊ አድርገዋል።
ከእነዚህ መካከል ሳን ፍራንሲስኮ ከተማ (ከዩ ኤስ ኤ) እና የካልጋሪ ከተማ (ከካናዳ) ተጠቃሾች ናቸው፡፡
በሳንፍራንሲስኮ ተግባራዊ የሆነው የኤስኤፍ ፓርክ (SF park) መርሃ ግብር በዘመናዊ ፓርኪንግ አስተዳደር ውስጥ ተጠቃሽ ነው፡፡ እ.ኤ.አ. በ 2011 የጀመረው መርሃ ግብሩ በትክክለኛ ፍላጎት ላይ በመመስረት የመኪና ማቆሚያዎችን መገንባትና ማስተዳደርን ታሳቢ ያደረገ አሰራር ነው፡፡
ይህ አሰራርም በከተማዋ ላይ አያሌ ለውጦችን አምጥቷል ይላል መረጃው። ለአብነትም የትራፊክ መጨናነቅን ቀንሷል፡- እ.ኤ.አ በ2014 የተደረገ ጥናት እንደሚያሳየውም አሽከርካሪዎች መኪናቸውን ለማቆም (ለፓርኪንግ) የሚያደርጉትን ጉዞ በ50 በመቶ እንዲቀንሱ አድርጓቸዋል፡፡ በዚህ ውስጥ የነዳጅ ፍጆታን፣ የአየር ብክለትን፣ የጊዜ ብክነትን፣ ትራፊክ መጨናነቅን እና መሰል ነገሮችን በግማሽ መቀነስ አስችሏል፡፡
ከላስ ቬጋስ እንማር (Learning from Las Vegas) በተሰኘው መፅሐፍ ላይ እንደተገለፀው በዘመናዊ የተሽከርካሪ ማቆሚያዎች ላይ ኢንቨስት ማድረግ ከፍተኛ ጥቅም ያስገኛል፡፡ ይህም የትራፊክ መጨናነቅን መቀነስ፣ የአካባቢ መሻሻል እና የኢኮኖሚ እድገትን ይጨምራል። በመሆኑም ከተሞች እድገታቸውን በሚቀጥሉበት ጊዜ እንደዚህ ያሉ አዳዲስ የመኪና ማቆሚያ ስርዓቶችን መተግበር ዘላቂ እና ቀልጣፋ የትራንስፖርት አውታሮችን ለመፍጠር ያግዛቸዋል፡፡
በሀርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ፕሬስ እ.ኤ.አ በ1941 የታተመው የጌዲዮን ሲግፍሪድ ቦታ፣ ጊዜ እና አርክቴክቸር (Space, Time and Architecture) የተሰኘው መፅሐፍ ላይ እንደሰፈረው በዓለማችን ብዙ መኪናዎች ባልነበሩበት ዘመን ሰዎች መኪናቸውን በጎዳናዎች ላይ እንዳሻቸው ያቆሙ ነበር፡፡
ይሁን እንጅ የመኪናዎች ቁጥር በከተሞች እየጨመረ፣ የሰውም ብዛት ከፍ እያለ ሲመጣ የመኪና ማቆሚያ ጉዳይ አሳሳቢ እየሆነ መጣ፡፡
በተለይም በገበያ ቦታዎች አብዛኛውን የመኪና ማቆሚያ ቦታ በሰራተኞች ብቻ መያዝ ጀመሩ፡፡ ይህም ለደንበኞች የሚሆን ቦታ እንዲጠፋ አደረገ፡፡ ይህንንም ተከትሎ በትላልቅ ከተሞች የትራፊክ መጨናነቅ ችግር የተለመደ ሆነ። ከመጨናነቅም ባሻገር በከተሞች የንግድ እና ልዩ ልዩ ስራዎች ላይ ማነቆ በመፍጠሩ የከተሞች ኢኮኖሚ መጎዳት ጀመረ፡፡
በመሆኑም የከተማ ህዝብ እየጨመረ ሲመጣ እና የትራፊክ መጨናነቅ እየተባባሰ ሲሄድ የዓለም ከተሞች በዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች የታገዙ የመኪና ማቆሚያ ስፍራዎችን ለመገንባት ተገደዱ።
ይህ ስልጡን የመኪና ማቆሚያ ስፍራ ዲጂታል የክፍያ ስርዓቶችን በመተግበር፣ መኪናዎችንም ሆነ የባለቤቶቹን ሙሉ አድራሻና ምስል የሚመዘግቡ እና መሰል መረጃዎችን ጭምር የሚይዙ ቴክኖሎጂዎችን ይጠቀማል፡፡
ለአብነትም የሳን ፍራንሲስኮ የዘመናዊ የመኪና ማቆሚያ ስርዓት በዓለም ላይ ካሉት የስማርት ፓርኪንግ ንቅናቄዎች አንዱ ነው። በከተማዋ ያሉ ሁሉም ፓርኮች ውስጥ ያለው እንቅስቃሴ በካሜራ ቁጥጥር ስር ነው፡፡
ይህም እንቅስቃሴ በሞባይል መተግበሪያዎች እና ድህረ ገጽ በኩል ለማህበረሰቡ ይጋራል፡፡ ይህም አሽከርካሪዎች ክፍት ቦታዎችን በፍጥነት እንዲያገኙ ያስችላቸዋል። በሌላ በኩልም ንብረታቸውን ባሉበት ቦታ ሆነው ይቆጣጠራሉ፡፡
ከተማዋ ይህን በማድረጓ ያለ አግባብ ክፍት ይሆን የነበረውን መኪና ማቆሚያ ቦታ 30 በመቶ መቀነስ ችላለች፡፡ ነዋሪዎቿም ለመኪና ማቆሚያ ደንቦች ተገዥ እንዲሆኑ አድርጋለች፡፡ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዋን አሳድጋበታለች። በነዋሪዎቿ ላይ ይደርስ የነበረውን የትራፊክና የአዕምሮ መጨናነቅ ቀንሳበታለች፤ ይላል ሳንፍራሲስኮ የፓርኪንግ አስተዳደር ተቋም በ2023 ይፋ ያደረገው መረጃ፡፡
የካናዳው ቪክቶሪያ ትራንስፖርት ፖሊሲ ተቋም የመኪና ማቆሚያ አስተዳደር ምርጥ ተሞክሮ (Parking Management Best Practices) ሲል እ.ኤ.አ ጥር 2018 ይፋ ባደረገው መረጃ መሰረት ዘመናዊ የመኪና ማቆሚያ ስፍራዎች የመኪና አደጋን በመቀነስ የዜጎችን ሕይወትና ንብረት ከአደጋ መታደግ አስችለዋል፡፡
እንደ መረጃው ከሆነ በመንገድ ላይ መኪናዎችን ማቆም በከተሞች የትራፊክ እንቅስቃሴ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ያሳድራል። እነዚህ ተፅዕኖዎችም የመንገድ አቅምን መቀነስ፣ መጨናነቅን መፍጠር፣ የካርቦን ልቀትን መጨመር እና በመንገድ ተጠቃሚዎች ላይ እስከ ሞት የሚያደርስ አደጋዎችን ይፈጥራል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ዘመናዊ የመኪና ማቆሚያዎች በከተሞች ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ያሳድራሉ፡፡ ለአብነትም ቀልጣፋ የፓርኪንግ አያያዝ የትራፊክ ፍሰትን ያሻሽላል፣ መጨናነቅን ይቀንሳል፣ ሰዎች የንግድ እንቅስቃሴዎች ላይ በቀላሉ እንዲሳተፉ ያደርጋል፡፡ የሀገር ውስጥም ሆኑ የውጭ ጎብኝዎች በከተሞች ያሉ የመስህብ ስፍራዎችን ጊዜያቸውን በአግባቡ ተጠቅመው እንዲጎበኙ ዕድል በመፍጠር ኢኮኖሚውን ከፍ ያደርጋል፡፡
በመለሰ ተሰጋ