የተቀናጁ የምግብ ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪዎችን ለማስፋት እየተሰራ ነው

You are currently viewing የተቀናጁ የምግብ ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪዎችን ለማስፋት እየተሰራ ነው

AMN- ጥቅምት 27/2017 ዓ.ም

የተቀናጁ የምግብ ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪዎችን ለማስፋትና የምግብ ምርትን ለመጨመር እየተሰራ መሆኑን የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል ገለጹ።

ከትናንት ጥቅምት 26 እስከ 28 ቀን 2017 ዓ.ም እየተካሄደ የሚገኘው “ከረሃብ ነፃ ዓለም” ዓለም አቀፍ ጉባዔ በዛሬው ዕለትም ቀጥሏል።

በጉባዔው የዛሬ ውሎ ኢንቨስትመንትን ማስፋፋትና የድኅረ-ምርት ብክነት ላይ ያተኮሩ የፓናል ውይይቶች ተካሂደዋል።

በዚሁ ጊዜም የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል፤ ኢትዮጵያ ጠንካራ የምግብ ሥርዓት ለመገንባት በቁርጠኝነት እየሰራች ነው ብለዋል።

በሀገሪቱ ባሉ የተቀናጀ የምግብ ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች የግብርና ምርቶችን በማቀነባበር የምርት ብክነትን ለመቀነስ፣ የቆይታ ጊዜያቸውን ለማራዘምና የሥራ ዕድል በመፍጠር የኢኮኖሚ እድገትን ለማረጋገጥ እየተሰራ ነው ብለዋል።

ይህም ለአርሶ አደሮች የገበያ ትስስርና ለበርካቶች የሥራ ዕድል የፈጠረ መሆኑን አንስተው፤ ይህም የመንግሥት፣ የግሉ ዘርፍና የአጋር አካላት ትብብር ድምር ውጤት ያለውን አስተዋፅዖ የሚያሳይ መሆኑን ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄም የግብርናና ኢንዱስትሪ ዘርፉን ማሳደግ የሚያስችሉ ሥራዎች መከናወናቸውን አስረድተዋል።

ኢትዮጵያ ዘላቂ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የምታደርገው ጉዞ የጋራ ጥረትና ኢንቨስትመንት የሚጠይቅ እንደሆነ አንስተው፤ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የግልና የመንግሥት አጋርነት ሚና ወሳኝ መሆኑንም መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review