
AMN-ጥር 7/2017 ዓ.ም
የጉምሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር ደበሌ ቃበታ በአምባሳደር ኡመር ሁሴን (ዶ/ር) የተመራ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የቢዝነስ ልዑክን በቢሮአቸው ተቀብለው አነጋግረዋል፡፡
ልዑካኑ በጉምሩክ ኮሚሽን ዋናው መስሪያ ቤት ጉብኝት ያደረጉ ሲሆን በኮሚሽኑ የሚሰጡ አገልግሎቶችን እና አገልግሎቱን ለማዘመን የተተገበሩ እና በመልማት ሂደት ላይ በሚገኙ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ዙሪያ ገለፃ ተደርጎላቸዋል።

የጉምሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር ደበሌ ቃበታ፤ ኮሚሽኑ አገልግሎቱን ለማዘመን የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን ተግባራዊ ያደረገ መሆኑን የገለጹ ሲሆን በርካታ የቴክኖሎጂ ውጤቶችንም በማልማት በቅርቡ ወደ ስራ ለማስገባት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
በቀጣይ በጉምሩክ ኮሚሽን ተግባራዊ የተደረጉ ሁሉንም የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ኢንትግሬት የማድረግ፣ ተጨማሪ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን የማልማት እና በሰው ሀይል አቅም ግንባታ ዙሪያ በትብብር መስራት እንደሚቻል ገልፀዋል፡፡

የቢዝነስ ልዑካኑን የመሩት በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች አምባሳደር ኡመር ሁሴን(ዶ/ር) የቢዝነስ ልዑካኑ በቴክኖሎጂው ዘርፍ በበርካታ ሀገራት ሰፊ ልምድ ያላቸው መሆኑን ገልፀው በቀጣይ በዝርዝር ጉዳዮች ላይ ውይይት በማድረግ እና በትብብር በመስራት የኮሚሽኑ የቴክኖሎጂ ፍላጎቶች ላይ ድጋፍ ለማድረግ ልዑኩ ዝግጁ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን ዘመናዊ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን እየተጠቀመ መሆኑን በመግለፅ በቀጣይ በኮሚሽኑ ዝርዝር የቴክኖሎጂ ፍላጎቶች ላይ በመወያየት በጋራ ለመስራት ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላቸውም ማረጋገጣቸውን ከኮሚሽኑ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡