AMN – የካቲት 4/2017 ዓ.ም
በኢትዮጵያ የተጀመረውን ሀገራዊ ምክክር በማጐልበት ከነጠላ ትርክት ይልቅ አሰባሳቢ ትርክቶች ላይ በትኩረት መስራት ይገባል ሲሉ የኢፌዴሪ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባዔ ሎሚ በዶ ገልፀዋል።
”ምክር ቤቶቻችን ለጠንካራ ሀገረ መንግስት ግንባታችን” በሚል ርዕስ በሰላም ሚንስቴር አዘጋጅነት በአዳማ ከተማ የውይይት መድረክ እየተካሂደ ነው።
የውይይት መድረኩን በንግግር የከፈቱት ምክትል አፈ-ጉባኤ ሎሚ በዶ የተጀመርነውን ሀገራዊ ምክክር በማጐልበት ከነጠላ ትርክት ይልቅ አሰባሳቢ ትርክቶች ላይ መስራት የሁሉም አካላት ቁልፍ ሚና መሆን እንደሚገባው አስገንዝበዋል፡፡
የቆየ የምክክር ባህላችንን በማሳደግ አኩሪ ባህልና እሴቶቻችንን በመጠቀም ከነጠላ ትርክት ይልቅ አሰባሳቢ ትርክቶች ላይ መስራት ይገባልም ብለዋል።
ምክትል አፈጉባዔዋ፣ በየጊዜው የሚነሱ የፖለቲካ ጥያቄዎች እና ሌሎች ጉዳዮች የሚስተዋሉ መሆኑን ጠቁመው፤ የተሟላ ሀገረ ብሄር ከመገንባት አኳያ ሰፊ ስራ መስራት እና መጠገን ያለባቸው ስብራቶች እንዳሉ አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ ህብረብሔራዊ የሆኑ ማንነቶችንና ልዩነቶችን በአግባቡ በመምራትና በማስተዳደር፤ አንድነቷን ጠብቃ በመጓዝ ፈርጀ ብዙ ታሪካዊ ሁኔታዎችን ማስተናገዷን ም አብራርተዋል፡፡
ዛሬ ላይ በሃገራችን የሚታዩ ችግሮችና የችግሮቹ መንስዔ በርካታ ቢሆኑም ችግሮችን ከስሩ ለመፍታት ጠንካራ ተቋማትን እና ብሔረ-መንግሥትን መገንባት ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው ብለዋል።

ምክር ቤቶች ህብረ-ብሔራዊ አንድነትን በማረጋገጥ እና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን በማጠናከር ረገድ ከፍ ያለ ሚና በመጫወት ላይ መሆናቸውንም ተናግረዋል።
የሰላም ሚኒስቴር ወቅታዊ ርዕሰ-ጉዳዮችን በማዘጋጀት በሀገራችን እየተስተዋሉ ያሉ ችግሮች ላይ ከምክር ቤቶች ጋር በቅርበት ለመምከር እና የመፍትሄ አቅጣጫ ለማመላከት እያደረገ ያለው እንቅስቃሴ የሚበረታታ መሆኑን ገልፀዋል።
በመድረኩ ምክትል አፈ ጉባዔ ሎሚ በዶን ጨምሮ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አመራሮችና አባላት፣ የፌዴሬሽን፣ የክልል፣ የከተማ አስተዳደርና የብሔረሰቦች ምክር ቤት አፈ ጉባዔዎች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች መገኘታቸውን ከምክር ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።