የታዳሽ ኃይልን በረከት የተቋደሱ ሀገራት

You are currently viewing የታዳሽ ኃይልን በረከት የተቋደሱ ሀገራት

ባለፉት ጥቂት አስርት ዓመታት ውስጥ ነዳጅን ብቻ በስፋት መጠቀም ዋጋ እንደሚያስከፍል ግልጽ እየሆነ መጥቷል። እ.ኤ.አ በ1950 በዓመት 5 ሚሊዮን ቶን የነበረው የካርቦንዳይኦክሳይድ ልቀት በ2020 ወደ 35 ሚሊዮን ቶን ደርሷል የሚለው መረጃ ደግሞ ለዚህ ሁነኛ ማሳያ ተደርጎ እየቀረበ ያለ ቁጥራዊ መረጃ ነው። ይህ አሃዝ ታዲያ እንዲሁ በጥሬው ሲተረጎም ዓለም በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ዋጋ እየከፈለች ስለመሆኑ አመላካች ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ በዚህም ሳቢያ ዓለም የታዳሽ ኃይል ኢኮኖሚ ከተሰኘ ሀሳብ ላይ የሙጥኝ እንድትል አስገድዷታል፡፡

በቦስተን ዩኒቨርሲቲ የዓለም አቀፍ ልማት ፖሊሲ ማዕከል የታዳሽ ኃይል ኢኮኖሚ ፍቺን ሲያብራራ እንዳስቀመጠው የታዳሽ ኃይል ኢኮኖሚ፣  እንደ ነዳጅ ባሉ ውስን ሀብቶች ላይ ብቻ የሙጥኝ ከማለት ተላቅቆ እንደ ፀሐይ፣ ንፋስ እና የጂኦተርማል  ኃይልና የተፈጥሮ ሀብቶች ላይ  የተመሰረተ የኢኮኖሚ ስርዓት ማለት ነው።

የታዳሽ ኃይል መሰረተ ልማት ግንባታ ደግሞ በባህሪው ለሌሎች የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች አመቺ ሁኔታን ከመፍጠር አልፎ በራሱ እንደ ትልቅ ኢኮኖሚ አንቀሳቃሽ ሆኖ ያገለግላል የሚሉት ደግሞ ‘The Economics of Renewable Energy’ መጽሐፍ ደራሲና የቦስተን ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎቹ ዴቪድ ቲሞንስ እና ጆናታን ሃሪስ ናቸው፡፡ ተመራማሪዎቹ ትልቅ ኢኮኖሚ አንቀሳቃሽ ሆኖ ያገለግላል የሚለውን ሀሳብ ሲያስረዱም ታዳሽ ኢኮኖሚ ለሌላ የኢኮኖሚ ዘርፍ ከሚሰጠው አገልግሎት በተጨማሪ ከፍተኛ ግምት የሚሰጠው የኢንቨስትመንትና የስራ እድልን ይፈጥራል። ሀገራት በየጊዜው የሚያድገውን የኃይል ፍላጎታቸውን ከማርካት አልፈው ከእነዚህ ታዳሽ ምንጮች ለዓለም ገበያ ጭምር ለሽያጭ ማቅረብ ያስችላል ይላሉ፡፡

በፈረንጆቹ በ2022 የወጣ መረጃ እንደሚያመላክተው ዓለም ከምትጠቀመው የኤሌክትሪክ ኃይል 30 በመቶ ያክሉ ከታዳሽ ምንጮች የሚገኝ ነው። ከታዳሽ አማራጮች የሚመነጭ የኤሌክትሪክ ኃይል መጠቀም አሁን አሁን በዓለማችን ላይ እየተለመደ የመጣ ሆኗል፡፡ እንደ ብራዚል፣ ኒውዚላንድ፣ ጃፓን፣ ሜክሲኮ፣ ኖርዌይ፣ ቬትናም ያሉ ሀገራት ደግሞ በዚህ ረገድ ተጠቃሽ ሀገራት ሲሆኑ፣ የተወሰኑትን በወፍ በረር ወደመቃኘቱ እንለፍ፡፡

እስያ የታዳሽ ኃይል እርምጃን በመምራት ቀዳሚ አህጉር ናት፡፡ አህጉሪቱ መንግስታትና የኢንዱስትሪ መሪዎች መሬት የረገጡ የታዳሽ ኃይል ኢንቨስትመንቶች እየተደረጉ ስለመሆናቸው የዓለም ባንክ መረጃ ያሳያል፡፡ በአህጉሪቱ እንደ ጃፓንና ቬትናም ያሉ ሀገራት ደግሞ ቀዳሚ ተጠቃሽ ሀገራት ናቸው፡፡

በተለይ ጃፓን ወደ ታዳሽና ንጹህ ኃይል የሚደረገውን ሽግግር ለመደገፍ እስከ 10 ቢሊዮን ዶላር የደረሰ በጀት ትመድባለች። ቶኪዮ ከጠቅላላ የኤሌክትሪክ ምርቷ 20 በመቶውን ከታዳሽ ኃይል፤ 7 በመቶውን ደግሞ ከኒዩክሌር ታገኛለች ይላል የሀገሪቱ ስታትስቲክስ ተቋም መረጃ፡፡ የጃፓን የታዳሽ ኃይል አቅርቦት በ10 ዓመት ውስጥ በ174 በመቶ እድገት ማሳየቱ ተገልጿል፡፡

የሩቅ ምስራቋ ጃፓን የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመግታት አበረታች ተግባር እየከወኑ ከሚገኙ ሀገራት ተርታ ትሰለፋለች። በዚህም በታዳሽ እና ንጹህ የኃይል ምንጭ ላይ የተወሰነና ከነዳጅ ጥገኝነት የተላቀቀ ኢኮኖሚ በመገንባት ላይ ትገኛለች።

የመንግስትም ሆነ የግል ተቋማት በካይ ከሆኑ የኃይል ምንጮች እንዲወጡም “ጃፓን ክላይሜት” የሚል የትብብር ማዕቀፍ አውጥታ ተግባራዊ ማድረግ ከጀመረች ከአስር ዓመት በላይ ሆኗታል። በዚህ ማዕቀፍ ውስጥም ከ700 በላይ ተቋማት አባል ሆነው በ2030 ከሚጠቀሙት የኤሌክትሪክ ኃይል ውስጥ ከ35 በመቶ በላዩ ከታዳሽ ኃይል ምንጮች እንዲሆን ስራዎች ቀጥለዋል ነው የተባለው። በ2050 ሙሉ በሙሉ ካርበን የማይበክላት ቶኪዮን እውን ለማድረግ የተቀመጡ ግቦችን እውን ለማድረግ የተወሰዱት እርምጃዎችም ከወዲሁ ውጤት እያስገኙ ነው። የሀገሪቱ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር መረጃ እንደሚያሳየው በ2021 ከጠቅላላ የጃፓን የኤሌክትሪክ ኃይል ምርት የታዳሽ ኃይል ምንጮች ድርሻ 20 በመቶ ደርሷል።

ከ2025 ጀምሮ በእያንዳንዱ ኩባንያ እና የግለሰብ መኖሪያ ቤት ጣሪያ ላይ የጸሐይ ኃይል ማመንጫ (ሶላር ፓኔል) እንዲሰቀል ለማድረግ እየሰሩ እንደሆነ የመንግስታቸው እቅድ ያሳያል። የጃፓን የኢኮኖሚ ሚኒስቴር መረጃ እንደሚያመለክተው ሀገሪቱ እስከ 2030 ባሉት ዓመታት የበካይ ጋዝ ልቀትን ለመቀነስ እስከ 132 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጡ ፕሮጀክቶችን ትጀምራለች ተብሏል። ሀገሪቱ ኃይድሮጅንን ኢኮኖሚዋን ከካርቦን ልቀት ለማላቀቅ እንደ ቁልፍ የኃይል አማራጭ አድርጋ ትመለከታለች።

ቅኝታችንን እዚያው እስያ ላይ ስናደርግ ወደ የኃይል ገበያ ብቅ ያለችውንና የእስያ የመጪው ጊዜያት የንፁህ ኃይል ቋት (Asia’s Next Clean Energy Powerhouse) በመባል የምትጠራውን ቬትናምን እናገኛለን፡፡ በቬትናም የታዳሽ ኃይል መጨመር ሀገሪቱን በዘላቂነት ዓለም አቀፍ መሪ ከፍተኛ ንጹህ የኢነርጂ ኢንቨስትመንት መዳረሻ አድርጓታል።

በቬትናም ኢኮኖሚ ላይ ጥናት ያደረጉትና የማርኬቲንግ ጉዳዮች ዓለም አቀፍ አማካሪው ቪክቶር ታቼቭ እንደሚሉት ባለፉት አስር ዓመታት የቬትናም የኤሌክትሪክ ፍላጎት ከእጥፍ በላይ ጨምሯል። በሀገሪቱ ጠንካራ የኢኮኖሚ እድገት፣ የህዝብ ቁጥር መጨመር፣ ከፍተኛ የኢንዱስትሪ እድገት እና የከተሞች መስፋፋት ደግሞ ዋነኛ ገፊ ምክንያቶች ስለመሆናቸው አማካሪው ያነሳሉ፡፡

ሀገሪቱ እያደገ ያለውን የኃይል ፍላጎት ለማሟላት ከድንጋይ ከሰል ኃይል ላይ ጥገኛ ሆና ብትቆይም በታዳሽ ኃይል ላይ መዋዕለ ንዋይ ፈሰስ ለማድረግ ከፍተኛ ትኩረት በማድረግ የኃይል ውህደቷን በማብዛት ረገድ ከፍተኛ መሻሻል አሳይታለች። በዚህም ሀገሪቱ ፈጣንና ንፁህ የኢነርጂ ሽግግር ለማድረግ፣ ቀጣይነት ያለው ዕድገት ለማስመዝገብና በታዳሽ ኃይል ዘርፍ የውጭ ኢንቨስትመንቶችን ለመሳብ ችላለች።

እ.ኤ.አ በ2014 በቬትናም የታዳሽ ኃይል ድርሻ 0 ነጥብ 32 በመቶ ብቻ የነበረ ሲሆን እ.ኤ.አ በ2015 ለኃይል ማመንጫ የሚሆን የተገጠመ የፀሐይ አቅም 4 ሜጋ ዋት ብቻ ነበር። አሁን 16 ነጥብ 5 ጊጋ ዋት የፀሐይ ኃይል አላት። በተያዘው የፈረንጆቹ ዓመት መጨረሻ የባህር ላይ ንፋስ በመጨመር ብቻ 12 ጊጋ ዋት ለማግኘት እየሰራች ትገኛለች፡፡ እ.ኤ.አ በ2015 እና 2023 መካከል የፀሐይ እና የንፋስ አቅም ለኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫነት የመጠቀም አቅማቸውም በአስር እጥፍ አድጎ 13 በመቶ ደርሷል።

በነፍስ ወከፍ የምትለቅቀው የካርቦን ልቀት ከዓለም አቀፉ አማካይ ያነሰ ቢሆንም አሁን ላይ ቬትናም ከ29 በመቶው የውሃ ኃይል ጋር በመደመር ኢኮኖሚዋን ከካርቦን ልቀት ለማላቀቅ አስተማማኝ ደረጃ ላይ ደርሳለች፡፡ እንደ ዓለም አቀፉ የታዳሽ ኃይል ኤጀንሲ (IRENA) መረጃ በ2021 ቬትናም በፀሐይ ኃይል የተገጠመ ከፍተኛ አቅም ካላቸው 10 ሀገራት ተርታ ትሰለፋለች። በ2030 የውሃ ኃይልን ሳይጨምርም የታዳሽ ኃይል ማመንጫዎች ድርሻ 31 በመቶ እና የንፋስ ኃይልን 18 ነጥብ 5 በመቶ ለማድረስ እየሰራች ትገኛለች፡፡ ቬትናም በፀሐይ ኃይል ብቻ በ2030 85 ጊጋ ዋት እና በ2050 ደግሞ 214 ጊጋ ዋት የመድረስ አቅም እንዳላት በጥናቱ ተረጋግጧል።

እነዚህ ስራዎች ታዲያ ሀገሪቱን በንፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች ላይ የሚደረጉ ኢንቨስትመንቶች ትልቅ አቅም ካላቸው ሀገራት ተርታ ስሟ እንዲጠቀስ አስችሏታል፡፡ አሁን ላይ ቬትናም በደቡብ ምሥራቅ እስያ ከሚገኙት ምርጥ የንፋስ ሀብት አመንጪዎች አንዷ እንድትሆን አስችሏታል፡፡

እ.ኤ.አ ከ2023 ጀምሮ ቬትናም እና በዓለም አቀፍ አጋሮቹ ቡድን (IPG) የዘጠኝ ሀገራት ቡድን ጋር ማለትም ከካናዳ፣ ዴንማርክ፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ኢጣሊያ፣ ጃፓን፣ ኖርዌይ እና ዩናይትድ ኪንግደም ከመሳሰሉ ሀገራት ጋር በመሆን በታዳሽ ኃይሉ ዙሪያ ጠንካራ ስራ እየሰራች ትገኛለች፡፡ በጥቅሉ በመላው ቬትናም የአረንጓዴ ኢነርጂ ኢንቨስትመንት ሁኔታ እንደሚያሳየው ሀገሪቱ በሚቀጥሉት ዓመታት ለንፁህ ኢነርጂ ፕሮጀክት ደጋፊ የገንዘብ ተቋማት ትኩረት ነጥብ ትሆናለች ተብሎ ይጠበቃል።

ማኪንሴይ ሰስተኔብሊቲ የተሰኘ ገጸ ድር መረጃ በታዳሽ ኢኮኖሚ መርህ እየተመራ ያለው መንገድ ለቬትናም ብዙ ዕድሎችን እየከፈተ ስለመሆኑ አስፍሯል። በሚቀጥሉት አምስት ዓመታትም አጠቃላይ የኃይል ወጪ 10 በመቶ መቆጠብ፣ 1 ነጥብ 1 ጊጋ ቶን የሙቀት አሟቂ ጋዝ ልቀትን መቀነስ እና ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ የኢነርጂ ምርቶችንም በ60 በመቶ መቀነስ ያስችላል ተብሎለታል። በእርግጥ ቬትናም አሁን ላይ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለንፁህ ኢነርጂ ኢንቨስትመንቶች ምቹነት በዓለም 11ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡ እንደ ቬቲን ኤስ.ሲ ባንክ ዘገባ ከሆነ የሀገር ውስጥ የታዳሽ ኃይል ገበያ ዋጋ 714 ቢሊዮን ዶላር የደረሰ ሲሆን ቢያንስ ለሚቀጥሉት 25 ዓመታትም እያደገ እንደሚሄድ ተገልጿል።

የቅኝታችንን መቋጫ በአውሮፓዊቷ ሀገር ኖርዌይ አድርገን ጥቂት መረጃዎችን እንመልከት፡፡ ከበለጸጉ ሀገራት ተርታ ስሟ የሚጠቀሰው ኖርዌይ 98 ነጥብ 5 በመቶ የሚሆነው የኤሌክትሪክ ኃይል የምታገኘው ከታዳሽ ምንጮች ነው፡፡ የዓለም ባንክ የሀገሪቱን የኢኮኖሚ ዕድገት አስመልክቶ ከዓመት በፊት ያስነበበው ሪፖርት እንደሚያሳየው በዓለም ላይ ቀዳሚ የታዳሽ ኃይልን አምራች ኖርዌይ ስትሆን 98 ነጥብ 5 በመቶ የሚሆነውን የኤሌክትሪክ ኃይል የምታገኘው ከታዳሽ ምንጮች ነው።

በሳህሉ ብርሃኑ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review