AMN – ታኅሣሥ 19/2017 ዓ.ም
የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ በኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሬሕይወት ታምሩ የተመራ ልኡካን ቡድን ጋር ሁለቱ ተቋማት በትብብር ለመስራት በሚችሉባቸው ጉዳዮች ላይ ውይይት አድርገዋል።
ዲጂታል ሄልዝ በጤና ሚኒስቴር ትኩረት ተሰጥቶት በጤና ፖሊሲ ውስጥ እንደተካተተ ያስረዱት የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ፤ ኢትዮ ቴሌኮም ለጤናው ዘርፍ እያቀረበ ስላለው የዲጂታል አገልግሎቶች ምስጋና አቅርበዋል፡፡
የቴሌኮም እና የዲጂታል መሰረተ ልማትን በመጠቀም በማህበራዊ ሚዲያ የጤና ትምህርት እና ትክክለኛ የጤና መረጃ ለማህበረሰቡ ማድረስ መቻሉን ዶ/ር መቅደስ ተናግረዋል፡፡
ጤና ሚኒስቴር የቴሌ ሄልዝ አገልግሎት በፖሊሲ እንዲደገፍ እና በህጋዊ መንገድ እንዲመራ እየሰራ ይገኛልም ብለዋል፡፡
በጤና ተቋማት የአገልግሎት ክፍያዎችን በቴሌብር ለመፈጸም የሚያስችል ሥራ እየተሰራ መሆኑንም አክለዋል፡፡
የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሬሕይወት ታምሩ በበኩላቸው፤ ኢትዮ ቴሌኮም በርቀት የሚገኙ ጤና ተቋማትን ጨምሮ የጤና ተቋማትን አሰራር በዲጂታል ቴክኖሎጂዎች በማዘመን፤ የአገልግሎት ጥራት መሻሻል ላይ በትኩረት እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡
የመንግስት ተቋማትን ጨምሮ በርካታ አገልግሎቶች በቴሌብር ማከናወን የሚቻልበት አሰራር ተግባራዊ መሆኑን የገለጹት ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ፤ ኢትዮ ቴሌኮም የጤና ተቋማትን ፍላጎት መሰረት ያደረገ የኔትወርክ እና የዲጂታል መሰረተልማት ማስፋፊያ የሚያደርግበትን የቴክኖሎጂ አማራጮች መለየቱን አስረድተዋል፡፡
በውይይቱ ጤና ሚኒስቴር እና የጤና ተቋማት እየተገለገሉባቸው የሚገኙት የመረጃ መሰብሰቢያ ስርአት (DHIS2)፣ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች የሚጠቀሙበት የመረጃ ስርአት (eCHIS)፣ የሰው ሃብት ማኔጅመንት ስርአት (IHRS) እና በጤና ተቋማት የወረቀት አልባ አሰራር ስርአት (EMR) ገለጻ ቀርቧል፡፡
በማጠቃለያውም የጤና ሚኒስቴር እና ኢትዮ ቴሌኮም ወደፊት በአጋርነት ሊሰሩ በሚችሉባቸው ጉዳዮች ዙሪያ በሰፊው ተወያይተው የጋራ ስምምነት ላይ መድረሳቸውን የጤና ሚኒስቴር መረጃ ያሳያል፡፡