የቴክኒክ እና ሙያ ኮሌጆች በቴክኖሎጂ እና በክህሎት የበለጸገ ትውልድ ከመፍጠር አኳያ ትልቅ ሃላፊነት እንደሚጠበቅባቸው ተገለፀ

AMN – ጥር 3/2017 ዓ.ም

ከተማዋ የጀመረችውን ሁለተናዊ ለወጥ ለማስቀጠል የቴክኒክ እና ሙያ ኮሌጆች በቴክኖሎጂ እና በክህሎት የበለጸገ ትውልድ ከመፍጠር አኳያ ትልቅ ሃላፊነት እንደሚጠበቅባቸው ተገለጸ

የቦሌ ማኑፋክቸሪን ኮሌጅም ከከፍተኛ፣ መካከለኛ እና አነስተኛ ኢንዱስትሪዎች ጋር በስራ ትስስር እና በስልጠና ትብብር ዙሪያ መክሯል፡፡

የኮሌጁ ዋና ዲን ዶክተር ታደሰ መኮንን ውይይቱ በኮሌጁ እና በኢንዱስትሪው መካከል ያሉ መልካም እድሎችን ለማስቀጠል እና እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት ያስችላል ብለዋል፡፡

ከተማዋ የጀመረችውን ለውጥ ለማስቀጠል የሰለጠነ የሰው ሃይል ያስፈልጋል ያሉት ዶክተር ታደሰ መኮንን ለዚህ ደግሞ ኮሌጆች ትልቅ ሃላፊነት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡

የለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ የስራና ክህሎት ጽ/ቤት ምክትል ሃላፊ ወ/ሮ ቤዛ ደመቀ ከኮሌጁ ጋር በእውቀት እና በክህሎት የበለጸገ ባለሙያ ለመፍጠር እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

ባለፉት 6 ወራት ከ12 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች አጫጭር ስልጠናዎችን በመስጠት ወደ ስራ እንዲገቡ መደረጉን ተናግረዋል፡፡

በኮሌጆች የሰለጠኑ በርካታ ዜጎች በኢንዱስትሪዎች የስራ እድል እየተፈጠረላቸው እንደሚገኝ የተናገሩት አምራቾች ከኮሌጁ ጋር በስራ ትስስር እና በስልጠና ትብብር የጀመሩትን ስራ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል፡፡

በመርሀ ግብሩም የተሻለ ትብብር ላደረጉ ኢንዱስትሪዎች እውቅና የተሰጠ ሲሆን በቀጣይ በሚከናወኑ ተግባራት ላይም የትብብር ስምምነት ተደርጓል፡፡

ቴዎድሮስ ይሳ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review