የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት መቀላጠፍ የወጪና ገቢ ንግድ ሚዛንን ለማስጠበቅ ወሳኝ ነው-ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር)

You are currently viewing የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት መቀላጠፍ የወጪና ገቢ ንግድ ሚዛንን ለማስጠበቅ ወሳኝ ነው-ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር)

AMN- መጋቢት 6/2017 ዓ.ም

ባቡርን ጨምሮ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎትን ቀልጣፋና ተደራሽ ማድረግ የወጪና ገቢ ንግድን ሚዛን ለማስጠበቅ ወሳኝ መሆኑን የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትሩ ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) ገለፁ።

በወጪ ንግዱ የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት ላይ ያሉ ዕድሎችና ተግዳሮቶች ላይ ያተኮረ ውይይት እየተካሄደ ነው።

ሚኒስትሩ በመድረኩ እንደገለጹት፤ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በወጪ ንግዱ ላይ መሻሻሎች ቢኖሩም አሁንም በርካታ ስራዎች ይቀራሉ።

ኢትዮጵያ ወደ ውጪ ከምትልካቸው ምርቶች ይልቅ የምታስገባቸው ይበልጣሉ ያሉት ሚኒስትሩ ይህም የንግድ ሚዛኑ እንዲዛባ ማድረጉን አንስተዋል።

ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስን ማቀላጠፍ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትን ለማሳደግና የንግድ ሚዛኑን ለመጠበቅ ወሳኝ መሆኑንም ተናግረዋል።

መንግስት የባቡር ትራንስፖርትን ጨምሮ በትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ዘርፉ የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችን ለመፍታት የሕግ ማዕቀፎችን ከማሻሻል ጀምሮ የተለያዩ መሰረተ ልማቶችን እያሟላ መሆኑን አብራርተዋል።

የወጪ ንግዱን ወጪ ቆጣቢና ቀልጣፋ በሆነ ሎጂስቲክስ ለማሳለጥም ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።

የኢትዮ ጅቡቲ ምድር ባቡር አክሲዮን ማህበር ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢንጅነር ታከለ ኡማ በበኩላቸው የባቡር አገልግሎቱን ፈጣን፣ ቀልጣፋና ወጪ ቆጣቢ በማድረግ የወጪ ንግዱ እንዲሳለጥ እየተሰራ ነው ብለዋል።

ተቋማቸው የወጪ ንግዱን ለማቀላጠፍ ከመሰረተ ልማት ጀምሮ ፈጣን አገልግሎት መስጠት የሚያስችሉ አሰራሮችን መዘርጋቱንም መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

የባቡር ትራንስፖርት ቡና፣ የቁም እንሰሳት፣ አትክልትና ፍራፍሬን ጨምሮ ለወጪ ንግድ ምርቶች ምቹና አስተማማኝ በመሆኑ ላኪዎች ከድርጅቱ ጋር እንዲሰሩ ጠይቀዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review