AMN – ጥር 21/2017 ዓ.ም
በተለያዩ ቦታዎች በመንቀሳቀስና የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ መስለው በተለምዶው “ሿሿ” የተባለውን ወንጀል ፈፅመዋል የተባሉ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታውቋል፡፡
ተጠርጣሪዎቹ ብዛታቸው 4 ሲሆን የወንጀል ድርጊቱን ፈፅመዋል ተብለው በቁጥጥር ስር የዋሉት በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ 5 አካባቢ መሆኑ ተገልጿል።
የግል ተበዳይ በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ቄራ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ሄደው የጤና ምርመራ ለማድረግ ዘነበወርቅ አደባባይ ትራንስፖርት እየጠበቁ እንደነበር ተመላክቷል።
ግለሰቦቹም በሰሌዳ ቁጥር ኮድ 2 B-13788 አ.አ በሆነ የቤት መኪና የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ መስለውና የግል ተበዳይን ተሽከርካሪው ውስጥ ካስገቧቸው በኃላ “ቄራ ድረስ ከምትሄጂ እዚሁ ቅርብ ቦታ የጤና ምርመራ ማድረግ ትችያለሽ፤ እናሳይሻለን” በማለት በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ 5 ታቦት ማደሪያ ተብሎ ከሚጠራው አካባቢ ሲደርሱ ቅያስ ውስጥ በማስገባት በእጅ ቦርሳ ውስጥ የነበረ 7900 ጥሬ ገንዘብ ይዘው ለመሰወር ሙከራ ሲያደርጉ በአየር ጤና አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ የፖሊስ አባላት በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ከአዲስ አበባ ፖሊስ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ግለሰቦቹ ወንጀሉን ፈፅመው በተሽከርካሪ ለማምለጥ በሚሞክሩበት ሰዓትም አንድ ግለሰብ ላይ አደጋ ማድረሳቸውን መረጃው ይጠቁማል።
ከተያዙት 4 ተጠርጣሪዎች ውስጥ አንዷ ሴት ስትሆን አስፈላጊው ምርመራ እየተጣራባቸው እንደሚገኝ የገለፀው ፖሊስ ግለሰቦቹ ከዚህ በፊትም በተመሳሳይ ወንጀል በጉለሌ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ፓስተር አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ ታስረው እንደነበርና ደጋጋሚ ወንጀል ፈፃሚዎች መሆናቸውን ጅምር የምርመራ መዝገቡ ያመለክታል።
የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ መስለውና የተለያዩ ማታለያ ዘዴዎችን በመጠቀም ወንጀሎችን የሚፈፅሙ ግለሰቦችን በህግ ለማስቀጣት ህብረተሰቡ የራሱን ጥንቃቄ ከማድረግ ጀምሮ ጥቆማ በመስጠት የተለመደውን ትብብር አጠናክሮ እንዲቀጥል የአዲስ አበባ ፖሊስ ጥሪውን እያስተላለፈ ተመሳሳይ ወንጀል የተፈፀመበት ካለ ኮልፌ በቀራኒዮ ክ/ከተማ ፖሊስ መምሪያ በመቅረብ ተጨማሪ መረጃ በመስጠትና ተጠርጣሪዎቹን በመለየት ተባባሪ እንዲሆን ፖሊስ መልዕክቱን አስተላልፏል።