የትግራይ ህዝብ የሚፈልገው ሰላም ነው – አቶ ጌታቸው ረዳ

You are currently viewing የትግራይ ህዝብ የሚፈልገው ሰላም ነው – አቶ ጌታቸው ረዳ

AMN – መጋቢት 4/2017 ዓ.ም

የትግራይ ህዝብ የሚፈልገው ሰላም ነው ሲሉ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጌታቸው ረዳ ገለጹ፡፡

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጌታቸው ረዳ የክልሉን ወቅታዊ ሁኔታ በማስመልከት ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

አቶ ጌታቸው በመግለጫቸው የትግራይ ህዝብ ላለፉት አራት ዓመታት በከፍተኛ ስቃይ ውስጥ ያለፈ በመሆኑ ከምንም በላይ ሰላም የሚያስፈልገው ህዝብ ነው ብለዋል፡፡

በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች የተቀጠፉበት ጦርነት ያስተናገደ ህዝብ እንደሆነና በኋላም በፕሪቶሪያው ስምምነት ወደሰላም የገባ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ይሁንና ያኔ ላይ ጦርነቱ እንዳይፈጠር በቂ ሥራ ያልሰራ አመራር ከጦርነቱ በኋላ በፕሪቶሪያ የተደረሰውን ስምምነት ተግባራዊ አድርጎ ወደተሟላ ሰላም ከመመለስ ይልቅ ክልሉን ዳግም ወደ ትርምስ ለማስገባት በመንቀሳቀስ አሁን ያለንበት ሁኔታ ላይ እንገኛለን በማለት ገልጸዋል፡፡

የትግራይ ህዝብ ሰላም ይፈልጋል፣ የትግራይ ወጣት ሰላም ይፈልጋል፣ መማር፣ ማደግ እና ሀብት ማካበት ይፈልጋል የሚለውንም በመግለጫቸው አንስተዋል።

የተፈጠረውን ሰላም ሁሉም አቅሙን ተጠቅሞ ማቆየት እንደሚፈልግም ተናግረዋል፡፡

ከጦርነት ትርፍ እናገኛለን ከሚል አባዜ ያልተላቀቀ ወይም በጥቅም የተሳሰረ ኃይል የትግራይን ህዝብ ሰላም የሚነሳ እንቅስቃሴ ውስጥ መግባቱን አመላክተዋል፡፡

ይህንን ሁኔታ ማስቆም በዋነኛነት የትግራይ ህዝብ ሥራ ቢሆንም፣ አሁን ባለን ሁኔታ የፕሪቶሪያው ስምምነት ተስማሚ የሆነው የፌደራል መንግስት እና ከዚህ ጉዳይ ጋር ቀጥታ ቁርኝት ያላቸው ዓለም አቀፍ አካላትም ማድረግ የሚገባቸውን ማድረግ እንዳለባቸው ጠቁመዋል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review