AMN – ታኅሣሥ 4/2017 ዓ.ም
“የኃላፊነት ጊዜዬ ከመጠናቀቁ በፊት አፍሪካ በጸጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ እንደሚኖራት ተስፋ አደርጋለሁ” ሲሉ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሀፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ ተናገሩ፡
ዋና ፀሀፊው በደቡብ አፍሪካ ጉብኝት እያደረጉ ይገኛል፡፡
በደቡብ አፍሪካ ዋና ከተማ ፕሪቶሪያ ከጋዜጠኞች ጋር በነበራቸው ቆይታ፣ “የጸጥታው ምክር ቤት በአሁኑ ሰዓት አምስት ቋሚ አባላት አሉት፤ ከአምስቱ መካከል ሁለቱ አፍሪካዊ መሆን አለባቸው” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ምክር ቤቱ 15 ቋሚና ተለዋጭ አባላት ያሉት ሲሆን ሩሲያ፣ ቻይና፣ አሜሪካ፣ ዩናይትድ ኪንግደምና ፈረንሳይ 5ቱ ቋሚ አባላት ናቸው፡፡
አልጀሪያ፣ ሞዛቢክና ሴራሊዮን ደግሞ ተለዋጭ አባል በመሆን በአሁኑ ሰዓት አፍሪካን የወከሉ ሀገራት ናቸው፡፡
ከ1 ነጥብ 5 ቢሊዮን በላይ ህዝብ የሚኖርባት የአፍሪካ አህጉር በተለያዩ ጊዜያት በጸጥታው ምክር ቤት የቋሚ መቀመጫ የማግኘት ጥያቄዎችን በመሪዎቿ በኩል ስታቀርብ መቆየቷ ይታወሳል፡፡
አፍሪካ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት በቋሚ መቀመጫ እንድትወከል የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተደጋጋሚ ጥሪ ማቅረባቸው ይታወቃል፡፡
የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎዛ በበኩላቸው፣ የጸጥታው ምክር ቤት የተወሰኑ ሀያላን ሀገራቷ ብቻ በቋሚ አባልነት ያቀፈ ሊሆን አይገባም፤ ተቋሙ ሪፎርም ያስፈልገዋል ሲሉ ሞግተዋል፡፡
ይህን ሀሳብ የሚጋሩት የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲንም አፍሪካ በምክር ቤቱ መቀመጫ ሊኖራት እንደሚገባ እና የበለጸጉት ቡድን 20 ሀገራት ስብስብም የአፍሪካን ፍላጎት ማንጸባረቅና ድምጻቸውም ጎልቶ እንዲሰማ የበኩሉን ሊወጣ ይገባል ብለዋል፡፡
የተመድ ዋና ጸሀፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ አሁን ያለውን የጸጥታው ምክር ቤት አወቃቀር ጊዜው ያለፈበት ነው በማለት በተደጋጋሚ ተቋሙን ተችተዋል፡፡አፍሪካን ያላገናዘበ ተቋማዊ ውክልናም ተቀባይነት የለውም ብለውም ያምናሉ፡፡
በነሐሴ ወር ላይ በኒውዮርክ ተካሄዶ በነበረው የተመድ ጉባኤ ምክር ቤቱ አፍሪካን በቋሚ አባልነት እንዲያካትት ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን ለዚህ የሚሆን ሪፎርም ሊደረግ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡
ዋና ጸሀፊው ከጋዜጠኞች ጋር ባደረጉት ቆይታ፣ አሁን ላይ ተቋሙ የሪፎርም ኮሚቴ በማቋቋም ወሳኝ የለውጥ ሥራዎች ላይ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል፡፡
“አፍሪካ በጸጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ ኖሯት ሳላይ የዋና ጸሀፊነት ሥልጣን ጊዜዬ እንደማያበቃ ተስፋ አደጋለሁ” ሲሉ ጉቴሬዝ መናገራቸውን ሩሲያ ቱዴይ ዘግቧል፡፡