የነባር ፓርኮች አዲስ ገፅታ

You are currently viewing የነባር ፓርኮች አዲስ ገፅታ

በአዲስ አበባ ከተማ ከሚገኙ ለህብረተሰቡ አገልግሎት እየሰጡ ከሚገኙ ነባር ፓርኮች መካከል አምባሳደር ፓርክ አንዱ ነው፡፡ “መሀል ከተማ ላይ የሚገኘው ዘለግ ባሉ ዛፎች የተከበበው ይህ ፓርክ፤ አረንጓዴ ስፍራውና ነፋሻማነቱ አረፍ ብለው እንዲዝናኑ ይጋብዛል፡፡ ለዚህም ነው ማረፍና ብቻዬን መሆን ስፈልግ ፓርኩን ምርጫዬ ያደረኩት፡፡ እንደዚህ አይነት ቦታዎችን ማዘውተር ደስ ይለኛል።” ሲሉ የነገሩን በፓርኩ ባለው መቀመጫ ወንበር አረፍ ብለው መጽሐፍ ሲያነቡ ያገኘናቸው የአዲስ አበባ ነዋሪው አቶ ሰለሞን በርሔ ናቸው፡፡

“በፓርኩ የሚሰጠው አገልግሎት ጥሩ ነው” የሚሉት አቶ ሰለሞን፤ ነገር ግን ካፍቴሪያው ህብረተሰቡ እንደሚፈልገው የሚሰጠውን አገልግሎት ማሳደግ፣ ዘመኑን የሚመጥን አገልግሎት ቢኖር፤ በተለይ ወጣቶች አልባሌ ቦታ እንዳይውሉ ቴኒስ፣ ከረምቡላ፣ ቼዝ፣ ዳማ ቢኖር ለተዝናኖት መልካም ይሆናል ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

ሌላኛው አቶ ነስሩ መሀመድም በዚሁ በፓርኩ ሲዝናኑ ነው ያገኝናቸው። “ፓርኩ ውስጥ ያሉ ዛፎች ለእይታ ማራኪ ናቸው፣ ፀጥታው ደስ ይለኛል፡፡ እዚህ ስመጣ የህሊና እርካታ ይሰማኛል፡፡ መፀዳጃ ቤቱም ንፁህ ነው፡፡ ህብረተሰቡ እንደዚህ አይነት ስፍራዎች እየመጣ ቢዝናና ያተርፍበታል” ሲሉ ሃሳባቸውን ሰንዝረዋል፡፡

የአምባሳደር ፓርክ ቡድን መሪ ወ/ሪት ህይወት ደበላ በሰጡት መረጃ፤ ፓርኩ ከመዝናኛነት ባለፈ የምግብ፣ የሻይና ቡና አገልግሎት፣ ለአካል ጉዳተኞች ዊልቸር (የተሽከርካሪ መኪና) ለሚጠቀሙ በሚመች መልኩ የተሰራ ደረጃውን የጠበቀ መፀዳጃ ቤት፣ ማረፊያ ቦታዎች፣ ለአይን ማራኪ የሆነ አረንጓዴ ስፍራ፣ የዋና ገንዳ፣ ሰውሰራሽ ፏፏቴ (ፋውንቴን)፣ የህፃናት መጫወቻ፣ ካፍቴሪያ፣ የውስጥ ለውስጥ የእግረኛ መንገድ ይገኙበታል። ከመዝናኛነት ባለፈ ለሰርግ፣ ለልደት ዝግጅት አገልግሎት የሚሰጥ መሆኑንና ለከተማው ነዋሪ የመዝናኛ አማራጭ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ከኮሪደር ልማቱ ጋር ተያይዞ እየለማ ይገኛል፡፡ በቀጣይ ቴኒስ፣ ተጨማሪ የህፃናት መጫወቻ፣ ቤተ መጻሕፍትና ሌሎች አገልግሎቶች ተሟልተው በእቅድ ይሰራሉ፡፡  በፓርኩ ለመዝናናትም ለአዋቂም ሆነ ለህፃናት ተመጣጣኝ መግቢያ ክፍያ ያለው ሲሆን፤ ከሰኞ እስከ አርብ ከ2፡30 እስከ 11፡30 ለህዝብ ክፍት ነው፡፡ ቅዳሜና እሁድ በተለየ እስከ 12፡30 ክፍት በመሆኑ ሁሉም ህብረተሰብ መጥቶ መዝናናት እንደሚችል ቡድን መሪዋ ገልጸዋል፡፡

ሌላው ቅኝት ያደረግንበት ነባር ፓርክ ሐምሌ 19 መናፈሻ ፓርክ ሲሆን፤ ከነገስታቱ ዘመን ጀምሮ ያሉ እድሜ ጠገብ ዛፎች ይገኙበታል፡፡ ስፍራው እጅግ ማራኪ ነው፡፡ ፀጥታውና ነፋሻማነቱ በስራ የዛለን አዕምሮ ለማደስ፤ ለህሊና እረፍትና ለአዕምሮ እርካታ የሚሰጥ ነው።

ወጣት ዮናታን ለገሰም በጥንታዊው ሐምሌ 19 መናፈሻ ፓርክ እየመጣ የመዝናናት፣ አዕምሮውን የማደስ ልምድ እንዳለው አጫውቶናል፡፡ ፓርኩ የካፌ አገልግሎት ምግብም ጭምር ይሰጣል። ሰፊ የአረንጓዴ ስፍራና የህፃናት መጫወቻ ይገኝበታል፡፡ ኪስን በማይጎዳ ዋጋ ከጓደኛ፣ ከቤተሰብ ጋር እንዲሁም ብቻውን መሆን ለሚፈልግ እዚህ መጥቶ ቢዝናና ፀጥታና ነፋሻማ በመሆኑ ሰላምን ይሰጣል ይላል፡፡ በተጨማሪነት ፓርኩ ሰፊ ቦታ ስላለው የዱር እንስሳት ቢኖሩ፣ ለወጣቶች መዝናኛ እንደ ቼዝ፣ ፑል ዓይነት መጫወቻዎች ቢኖር የበለጠ የሚጎበኝ ስፍራ ያደርገዋል በማለት ወጣት ዮናታን ሃሳቡን ገልጿል፡፡

ሐምሌ 19 መናፈሻ ፓርክ የተመሰረተው በአፄ ኃይለስላሴ ዘመን በ1933 ዓ.ም ሲሆን በወቅቱ ለንጉሳዊያን ቤተሰብ ብቻ ነበር የሚያገለግለው፡፡ ለህዝብ መዝናኛነት ክፍት የሆነው በደርግ ዘመን ሐምሌ 19 ቀን 1967 ዓ.ም ነው፡፡ በዚህ ምክንያትም ስያሜውን ማግኘቱን  የፓርኩ ቡድን መሪ አቶ ፉአድ ሀሰን ገልፀዋል፡፡

በግቢው የአፄ ኃይለስላሴ ባለቤት የእቴጌ መነን ማረፊያ ቤት እና ሌሎች ጥንታዊ ቤቶች ይገኙበታል፡፡ እድሜ ጠገብ አረንጓዴ ዛፎች፣ ውብ አበቦች፣ የእግረኛ መንገድ፣ ከ33 በላይ ለሰርግ፣ ለፎቶ መርሀ ግብር ለልደትና ለተለያዩ ማህበራዊ አገልግሎት የሚውሉ ደሴቶች (የተለዩ ስፍራዎች)፣ የህፃናት መጫወቻና ካፍቴሪያ አሉት፡፡ በፓርኩ ከ102 ዓይነት በላይ ዝርያ ያላቸው ሀገር በቀልና የውጭ የጥላ ዛፍና አበቦችም ይገኛሉ፡፡ በነዚህ ተክሎች ላይ ከዩኒቨርሲቲዎች፣ ከውጭ ሀገራት፣ ከጉለሌ እፅዋት ማዕከል እየመጡ ጥናትና ምርምር እንደሚያደርጉም አቶ ፉአድ ጠቁመዋል፡፡

አቶ ፉአድ እንደሚገልፁት፣ ዘመናዊ የህፃናት መጫወቻ፣ የመዋኛ ገንዳ እንዲኖር እንዲሁም እግረኛ መንገድን ለማዘመንና ግቢውን የበለጠ ለማስዋብ እቅድ ተይዟል፡፡ ሐምሌ 19 መናፈሻ ፓርክ ታሪካዊነቱን ጠብቆ እንደ አዳዲስ ፓርኮች አስፈላጊው መሰረተ ልማት ቢሟላለት፣ የውሃ አቅርቦቱ ቢሻሻል፣ እድሳት ቢደረግለት ከጥንታዊነቱ አንፃር የቱሪስት መዳረሻ ስለሚሆን የሚመለከተው አካል ቢያስብበት ሲሉ ሃሳባቸውን አቅርበዋል።

ፓርኩ በ1974 ዓ.ም ክፍያ ሲጀምር መግቢያ ለተማሪ 25 ሳንቲም፣ ስራ ላለው 50 ሳንቲም ሆነ፡፡ በአሁኑ ወቅት ከእሁድ እስከ እሁድ ከ2፡30 እስከ 11፡30 አገልግሎት የሚሰጥ ሲሆን ለአዋቂ 30 ብር፤ ለህፃናት 20 ብር እንዲሁም ለውጭ ዜጋ አዋቂ 100 ብር፤ ለውጭ ዜጋ ህፃናት ደግሞ 50 ብር መሆኑንና ከሁሉም ፓርኮች በጣም ዝቅተኛ ዋጋ መሆኑን አቶ ፉአድ ይናገራሉ፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ የህዝብ መዝናኛ ቦታዎች አስተዳደር ኮርፖሬሽን ምክትል ስራ አስፈፃሚ አቶ ዋለልኝ ደሳለኝ በበኩላቸው ለጋዜጣው ዝግጅት ክፍል በሰጡት መረጃ፤ ኮርፖሬሽኑ በከተማዋ ያሉ ነባር እና አዳዲስ ፓርኮችን የሚያስተዳድር እንደመሆኑ አገልግሎታቸውን ለማሻሻል የሚያስችሉ መሰረተ ልማቶች እንዲሟሉላቸው የማድረግ ስራዎችን በማከናወን ህብረተሰቡ ከፓርኮች የሚያገኘውን ጥቅም ከፍ እንዲል ጥረት እየተደረገ ይገኛል፡፡ በከተማዋ 23 ነባር ፓርኮች ይገኛሉ፡፡ ፓርኮቹ ሰፊ ቦታ የያዙና የተከለሉ ቦታዎች ሲሆኑ፤ በውስጣቸው ለአዋቂና ለህፃናት የሚሆኑ በአረንጓዴ ተክሎች የተከበቡ፣ የመዝናኛ ስፍራ፣ አነስተኛ ካፍቴሪያ፣ ማህበራዊ ጉዳዮች የሚከወንበት አዳራሾችን ያካተቱ ሲሆን፤ የሰርግና ሌሎች የመዝናኛ አገልግሎትም ይሰጡ እንደነበር ገልፀዋል፡፡

እንደ ምክትል ስራ አስፈፃሚው ገለፃ፤ አብዛኛው ነባር ፓርኮች የሚጠበቅባቸውን አገልግሎት ለመስጠት የሚያስፈልጓቸው መሰረተ ልማቶች በአግባቡ ሳይሟላላቸው ከስልሳ ዓመታት በላይ የቆዩና በሚፈለገው ደረጃ ማሻሻያ ያልተደረገባቸው ናቸው፡፡ ለምሳሌ የመፀዳጃ ቤት በተገቢው አለመኖር፣ የህፃናት መጫወቻዎች ከፊሎቹ የተሰባበሩ ወይም ያልነበሩበት፣ ከደህንነት ጋር ተያይዞ የጥበቃ አገልግሎትና ሌሎችም በተሟላ ሁኔታ ያልነበራቸው ነበሩ፡፡

በመሆኑም ያሉባቸውን ክፍተቶች ለማሻሻል የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ነው፡፡ ለአብነት የፓርኮቹን ምድረ ግቢ የማስዋብ እና የአረንጓዴ ልማት ስራ መስራት፣ ሰው ሰራሽ ፏፏቴ (ፋውንቴን) እንዲኖራቸው ማድረግ፣ የውሃ አቅርቦት ለማሻሻል ጥልቅ ውሃ ጉድጓዶችን የመቆፈር፣ የመፀዳጃ ቤት አገልግሎት፣ በፓርኮች ውስጥ የሚገኙ የሚጎበኙ የዱር እንስሳት አይነታቸውና ቁጥራቸው እንዲጨምር የማድረግ፤ ለምሳሌ በፒኮክ ፓርክ ውስጥ ተጨማሪ አንበሳ እንዲገባ የማድረግና ሌሎችም ስራዎች ተሰርተዋል፡፡ በራስ አቅምና ከግል ዘርፉ ጋር በመቀናጀት  የፓርኮቹን መሰረተ ልማት ለማሻሻል ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

አቶ ዋለልኝ እንዳስረዱት፤ በተሰራው ስራ ለህብረተሰቡ የተሻለ አገልግሎት እየሰጡ ያሉ ፓርኮች ለአዋቂም ለህፃናትም የሚሆኑ አስፈላጊ የሆኑ መሰረተ ልማቶች ማለትም አረንጓዴ መዝናኛ ስፍራ፣ የመኪና ማቆሚያ፣ የህፃናት መጫወቻ ስፍራ፣ ማንበቢያ ስፍራ፣ ደረጃቸውን የጠበቁ መፀዳጃ ቤትና ሌሎችም አገልግሎቶች የተሟሉላቸው ናቸው። በአሁኑ ወቅት የማሻሻያ ስራ እየተሰራ የሚገኝባቸው ፓርኮች በመኖራቸው ሁሉም ነባር ፓርኮች በተመሳሳይ ደረጃ አገልግሎት እየሰጡ ነው ማለት እንደማይቻልም ያነሳሉ፡፡ ፒኮክ ፓርክ፣ ኢትዮ-ኩባ ፓርክ፣ ብሔረ ፅጌ፤ የቢትወደድ ወልደፃዲቅ ጎሹ መታሰቢያና ሌሎችም ፓርኮች የተሻለ አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ፡፡ የኮሪያ ዘማቾች መታሰቢያ ፓርክ የማሻሻያ ስራ እየተሰራ ካለባቸው ፓርኮች ይጠቀሳል፡፡

የጋዜጣው ዝግጅት ክፍል ተዘዋውሮ ከቃኛቸው ነባር ፓርኮች መካከል አምባሳደር ፓርክ አገልግሎቱ ቀዝቀዝ ብሏል፡፡ በተለይ የካፍቴሪያ የምግብ አቅርቦቱ መሻሻል እንዳለበት በፓርኩ ሲዝናኑ አግኝተን ያነጋገርናቸው ነዋሪዎች አንስተዋል፡፡ እንዲሁም ሐምሌ 19 መናፈሻ ፓርክ የተሻለ ቢሆንም የህፃናት መጫወቻ ቁሳቁሶቹ ዘመኑን የማይመጥኑና ያረጁ እንደሆኑ ተመልክተናል፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ምንድነው? ብለን ላነሳንላቸው ጥያቄ አቶ ዋለልኝ በሰጡት ምላሽ “በከተማዋ እየተሰራ ባለው የኮሪደር ልማት አብረው እየለሙ የሚገኙ ናቸው። እነዚህም ከእንጦጦ ተነስቶ እስከ ፒኮክ ባለው 21 ኪሎ ሜትር በሚሸፍን የወንዝ ዳርቻ ልማት መስመር ውስጥ የሚገኝ እንጦጦ ፓርክ፣ የኮሪያ ዘማቾች መታሰቢያ ፓርክ፣ ወዳጅነት ፓርክ፣ አምባሳደር ፓርክ፣ ኢሬቻ ፓርክ፣ እና ፒኮክ ፓርክ በወንዝ ዳርቻው እየለሙ ይገኛሉ፡፡ በተመሳሳይ ከሽሮ ሜዳ እስከ አራት ኪሎ የኮሪደር ልማት መስመር ስድስት ኪሎ የሚኘው አንበሳ ግቢ እየለማ ነው፡፡ ሐምሌ 19 ፓርክም በቀበና የወንዝ ዳርቻ ልማት ውስጥ ተካቶ የሚለማ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ አምባሳደር ፓርክና ሌሎችም በወንዝ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክት ማስፋፊያና ማሻሻያ ስራ እየተሰራላቸው ከመሆኑ ጋር ተያይዞ አሁን ባለው ሁኔታ የተነሱት እጥረቶች እንዳሉባቸው ይታወቃል፡፡ ሆኖም የኮሪደር ልማቱ ስራ ሲጠናቀቅ የፓርኮቹ የማሻሻያ ስራ አብሮ ስለሚጠናቀቅ የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት ያስችላቸዋል፡፡ በኮሪደር ልማት በርካታ ፓርኮች የሚሻሻሉበት ሁኔታም እየተፈጠረ ነው፡፡” ብለዋል፡፡

ነባር ፓርኮች በመሰረተ ልማቶቻቸው ዘመኑን የሚመጥኑ ሆነው አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ ምን እየተሰራ ነው? ላልናቸው ምክትል ስራ አስፈፃሚው ሲገልፁ፤ ነባር ፓርኮች ረጅም ጊዜ የቆዩ በመሆናቸው ከፍተኛ ኢንቨስትመንት የሚጠይቁ ናቸው፡፡ ከዚህ ባለፈ አሁን ያለውን የሰው ሃይል ጊዜውን የሚመጥን አገልግሎት የመስጠት ልምድ ያለው ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ አንፃር በቀጣይ በነባር ፓርኮች አስፈላጊውን መሰረተ ልማቶች በማሟላት፣ ህብረተሰቡ የሚፈልጋቸውን አገልግሎቶች በማቅረብ ወቅቱን እንዲመጥኑ ደረጃቸውን ከፍ የማድረግ እንዲሁም ጎን ለጎን የሰው ሃይሉንም አቅም የማጎልበት ስራ በእቅድ ተይዞ በትኩረት የሚሰራ ሲሆን፤ እነዚህ ተግባራት በራስ አቅም ብቻ ስለማይሆን ከባለድርሻ አካላት በተለይ ከግሉ ዘርፍ ጋር በትብብር የሚከወን መሆኑን በምላሻቸው ጠቁመዋል፡፡

አዲስ አበባ ከተማ ከነባር ፓርኮች ባለፈ በአሁኑ ወቅት ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ የህዝብ መናፈሻዎችና መዝናኛ ፓርኮች ባለቤት ናት፡፡ ከሀገር ባለፈ የውጭ ሀገር ቱሪስቶችን ቀልብ  መሳብ የቻሉ ፓርኮች ይገኙባታል። ለአብነት እንጦጦ ፓርክ ደረጃቸውን የጠበቁ በርካታ ሆቴሎች፣ ካፍቴሪያዎች፣ ሎጆች፣ የተለያየ ኩነት ማዘጋጃ የሚሆኑ ስፍራዎች፣ አምፊ ቴአትር፣ በቂ የሆነ የውሃ አቅርቦት፣ የመጫወቻ ስፍራና ሌሎችም አገልግሎቶች አለው፡፡ አንድነት፣ ወዳጅነት ቁጥር አንድና ሁለት ፓርኮችም ደረጃቸውን ጠብቀው የተሰሩና መሰረተ ልማቶች የተሟሉላቸው ናቸው፡፡

ኮርፖሬሽኑ ነባር ፓርኮችን ብቻ ሳይሆን በኮሪደር ልማት የለሙ አረንጓዴ ቦታዎችና ፕላዛዎችን በመረከብ እያስተዳደረ ይገኛል፡፡ በመጀመሪያው የኮሪደር ልማት የለሙ 33 የህዝብ መዝናኛ ቦታዎችንም በመረከብ እያስተዳደረ እንደሚገኝ ነው አቶ ዋለልኝ የሚገልፁት፡፡

“ከፍተኛ ሃብት የፈሰሰባቸው የከተማዋ ፓርኮች መገንባታቸው ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ ታስቦ ነው፡፡ በመሆኑም ነዋሪው በህዝብ መናፈሻና መዝናኛ ስፍራዎች ሲገለገል ፓርኮቹን መንከባከብ፤ እንደራሱ አድርጎ መጠበቅ አለበት፡፡ ይህ ተግባር የሁሉም ዜጋ ኃላፊነት መሆን አለበት” ሲሉ አቶ ዋለልኝ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በመዲናዋ የሚገኙ ነባር ፓርኮች በተመጣጣኝ ዋጋ አገልግሎት የሚሰጡ ሲሆኑ ለከተማዋ ነዋሪዎች አማራጭ የመዝናኛ ስፍራ ከመሆን ባሻገር ለመስህብነት እንዲሁም ለዜጎች የስራ ዕድል በመፍጠር ረገድ ከፍተኛ ፋይዳ አላቸው፡፡ በተለይ ነባር ፓርኮች የሚያስፈልጋቸውን መሰረተ ልማቶች በማሟላት፣ ዘመኑን የሚመጥኑ አገልግሎቶችን በማካተት፣ በከተማዋ አማራጭ የቱሪስት መዳረሻ ስፍራ እንዲሆኑ የተጀመረውን ተግባር አጠናክሮ መቀጠል ያስፈልጋል መልዕክታችን ነው።

በሰገነት አስማማው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review