AMN – ጥር 8/2017 ዓ.ም
በቃላችን መሰረት አዲስ አበባን እንደ ስሟ ውብ እና አዲስ ለማድረግ 24/7 በመስራት የነዋሪዎቻችንን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ እና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ የሚያደርጓት አስደናቂ ስራዎች ተከናዉነዋል ሲሉ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡
በአዲስ አበባ ሲካሄድ የቆየው የብልፅግና ፓርቲ ሁለተኛ መደበኛ ጉባኤ ቅድመ ጉባኤ ኮንፈረንስ ተጠናቋል፡፡
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በማህበራዊ የትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልእክት “ከቃል እስከ ባህል!” በሚል መሪ ቃል በአዲስ አበባ ሲካሄድ የቆየው የብልፅግና ፓርቲ ሁለተኛ መደበኛ ጉባኤ ቅድመ ጉባኤ ኮንፈረንስ የማጠቃለያ መድረክ ተከናውኗል ብለዋል፡፡
የብልፅግና ፓርቲ ኢትዮጵያን የማበልጸግ ራዕይ ሰንቆ ከየትኛዉም ዋልታ ረገጥ እሳቤ ርቆ ሚዛናዊ የመሃል ፓለቲካ እሳቤን በመከተል ተግባቦት ላይ የተመሰረተ የዳበረ የዴሞክራሲ ባህልን መገንባት፣ አካታች እና ሰው ተኮር ስራዎችን በመተግበር የኑሮ ጫና የሚያቀሉ እና ሀገር የሚያበለፅጉ ስራዎችን በመስራት ቃልን በተግባር እየፈፀመ ያለ ግዙፍ ፓርቲ ነዉ ብለዋል።
በብዙ ውጣ ውረድ ውስጥ አልፎ እስከ ዛሬ ድረስ በሀገር ዉስጥና በዉጪ የተመዘገቡ ድሎችን የተጎናፀፈዉ በፅናት እየተራመደ ከህዝባችን ጋር በትብብር በሰራዉ ስራ ነዉ ሲሉም አመልክተዋል።
የምንሰራው ስራ የሀገራችንን ዘላቂ ልማት እና ሰላም የሚያረጋግጥ በመሆኑ በቀጣይም ከህዝባችን ጋር በመሆን የኢትዮዽያን ብልፅግና ለማረጋገጥ ተግተን መስራታችንን አጠናክረን የምንቀጥል ይሆናል ብለዋል በመልእክታቸው፡፡