AMN – ጥር 8/2017 ዓ.ም
የግብዓት አቅርቦት ሰንሰለቱ እንዲያጥር በማድረግ የኑሮ ውድነትና የዋጋ ግሽበት ለመቀነስ በበጀት ዓመቱ ግማሽ ዓመት 217 የእሁድ ገበያ መዳረሻዎች ወደ ተግባር መግባታቸውን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ አስታወቀ፡፡
ቢሮው የ2017 ዓ.ም የመጀመሪያ ግማሽ ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ላይ ውይይት አካሂዷል፡፡
ቢሮው በበጀት ዓመቱ ግማሽ ዓመት ከንግድ ምዝገባና ዕድሳት አንፃር 31ሺህ 267 መፈፀሙ ተመልክቷል፡፡
ለ46 ሺህ 002 የንግዱ ማህበረሰብ አዲስ የንግድ ሥራ ፈቃድ አገልግሎት መስጠቱ የተገለጸ ሲሆን ለ411ሺ 548 ነጋዴዎች የንግድ ሥራ ፈቃድ እድሳት አገልግሎት መስጠቱ ተገልጿል፡፡
የግብዓት አቅርቦት ሰንሰለቱ እንዲያጥር በማድረግ አቅርቦትን በማሳለጥ የኑሮ ውድነትና የዋጋ ግሽበትን ለመቀነስ የሚያስችሉ ስራዎች መከናወናቸው የተነሳ ሲሆን በዚህም 217 የእሁድ ገበያ መዳረሻዎች ወደ ተግባር መግባታቸው ተጠቅሷል፡፡
ከንግድ ቁጥጥርና ክትትል አኳያም በ225 ሺህ 306 የንግድ ድርጅቶች ላይ የበር ለበር ክትትል እና ቁጥጥር በማድረግ የንግድ ህገ-ወጥነትን የመከላከል ስራ መሰራቱ ተነግሯል፡፡
የ131ሺህ 250 ነጋዴዎች የንግድ ምዝገባና ፈቃድ ማህደሮች ኦዲት መደረጋቸው ተመልክቷል፡፡
በዚህም በህገ-ወጥ የንግድ ሥራ ላይ ተሰማርተው በተገኙ የንግድ ድርጅቶች ላይ እርምጃ መወሰዱን እና የነዳጅ ስርጭት ቁጥጥሩም የተሻለ መሆኑ ተመለክቷል፡፡
ለስራ ምቹ አካባቢን የመፍጠር፣ የተግባቦትና የህዝብ ግንኙነት ስራዎች፣ ሌብነትና ብልሹ አሰራርን መግታት ፣ የሸማቾች መብት ማስጠበቅ እና ህገ ወጥ የዋጋ ንረትን በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ ቢሮው አመርቂ ውጤት ያሳየባቸው መሆኑ ተነስቷል፡፡
በውይይቱ ላይ ከወረዳ እስከ ማዕከል የሚገኙ አመራሮች መሳተፋቸውን ከቢሮው የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡