
AMN – ጥቅምት 28/2017 ዓ.ም
የአሜሪካው ኮንግረንስ እአአ በመጪው ጥር 6 ተገናኝቶ ዶናልድ ትራምፕ የ2024ቱ የሀገሪቱ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ አሸናፊ መሆናቸውን እንደሚያፀድቅ ተገልጿል።
በአጠቃላይ እአአ ታኅሣሥ 17/2024 ሁሉም ግዛቶች የተሰጡ ድምጾችን ውጤት በማስረከብ አሸናፊው ተወዳዳሪ ይፋ ይሆናል።
ከዚያም የአሜሪካ ኮንግረንስ እአአ ጥር 6/2025 ተገናኝቶ በተሰጠው ድምፅ መሠረት የአዲሱን ተመራጭ ፕሬዚዳንት ሥልጣን ያጸድቃል።
ተሸናፊዋ ተወዳዳሪ ካማላ ሐሪስ በዚህ ሥርዓት ላይ ይታደማሉ ተብሏል።
በቀጣይም ትራምፕ ሥልጣናቸውን ከጆ ባይደን የሚረከቡ ሲሆን፣ የሥልጣን ርክክብ ሥርዓቱን በሚያዘጋጁ አካላት በነጩ ቤተመንግሥት በደማቁ ይከናወናል።
ትራምፕ ምክትላቸውን እና ሌሎች ባለሥልጣናትንም ይፋ ያደርጋሉ።
ተሰናባቹ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር በማድረግ ሥርዓቱን ደማቅ ያደርጉታል ተብሎ ይጠቃል።
ከሥልጣን ርክክቡ በኋላ ትራምፕ ወዲያውኑ ሥራቸውን እንደሚጀምሩ ተነግሯል።
የዶናልትራምፕ ተፎካካሪ የነበሩት ካማላ ሐሪስ የትራምፕን አሸናፊነት እንዲቀበሉ ደጋፊዎቻቸውን መማፀናቸውን የቢቢሲ ዘገባ ያመላክታል።
ዶናልድ ትራምፕ በአሜሪካ ታሪክ ባለፉት 130 ዓመት ውስጥ በተለያዩ የምርጫ ጊዜያት ፕሬዚዳንት ሆኖ ዳግም ወደ ነጩ ቤተመንግሥት የተመለሰ ፕሬዚዳንት ሆነዋል።
ትራምፕ ገና በቅጡ ማሸነፋቸው ሳይረጋገጥ ነበር ብዙዎቹ የዓለም መሪዎች የእንኳን ደስ ያለዎት መልዕክት ያደረሷቸው።
በዚህ በኩል የእስራኤሉን ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁን እና የእንግሊዙን ጠቅላይ ሚኒስትር ኬር ስታርመር የቀደማቸው አልነበረም።
ዶናልድ ትራምፕ በሰሜን ካሎራይና፣ ጆርጂያ፣ ፔንሲሊቬኒያ እና ዊስኮንሲን ትራምፕ እንደሚያሸንፉ ትልቅ ግምት ነበር። እናም በእነዚህ ግዛቶች ባገኙት 270 ድምፅ አሸናፊነታቸውን ማረጋገጥ ችለዋል።