የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የትራምፕ አስተዳደር በስህተት ኤል-ሳልቫዶር ወደሚገኝ እስር ቤት የላከውን ግለሰብ እንዲመልስ ትዕዛዝ አስተላልፏል።
የትራምፕ አስተዳደር ኪልማር አብሬጎ ጋርሲያ የተባለው ግለሰብ “በአስተዳደራዊ ስህተት” ምክንያት ወደ ኤል ሳልቫዶር መላኩን ቢያምንም የግለሰቡን መመለስ “እንደሚያመቻች እና እንዲያስፈፅም” የተባለውን ውሳኔ ይግባኝ እንደሚጠይቅበት አስታውቋል።
ሐሙስ ዕለት ዘጠኙም የጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኞች በአንድ ድምፅ የግለሰቡን መመለስ አስተዳደሩ እንዲያስፈፅም አዘዋል።
ከኤል ሳልቫዶር ተሰዶ ወደ አሜሪካ የመጣው ጋርሲያ ባለፈው ወር በአውሮፕላን ተጭነው ወደ ኤል ሳቫዶሩ አስፈሪ እስር ቤት ሴኮት ከተላኩ ግለሰቦች መካከል ነው።
ይህ እስር ቤት ኤል ሳቫዶር እና አሜሪካ በገቡት ስምምነት መሰረት አደገኛ የሚባሉ የወንበዴ ቡድን አባላት የሚታሰሩበት ነው።
የትራምፕ አስተዳደር ምንም እንኳ ጋርሲያ “በአስተዳደር ስህተት ምክንያት ነው” ወደ ኤል ሳልቫዶር የተላከው ቢልም ግለሰቡ ኤምኤስ-13 የተባለው የወንበዴ ቡድን አባል ነውም ይላል። የጋርሲያ ጠበቃ ግን ይህን ያስተባብላሉ።
የጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኞች የትራምፕ አስተዳደር በምን ያክል ጊዜ ጉዳዩን እንደሚያስፈፅም ያሉት ነገር የለም።
ጋርሲያ በአውሮፓውያኑ መጋቢት 15 በቁጥጥር ሥር ውሎ ወደ ኤል ሳልቫዶር መላኩን በማስታወስ የዘገበው ቢቢሲ ነው።