የአሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫው እንዴት እየተሰጠ ነው?

You are currently viewing የአሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫው እንዴት እየተሰጠ ነው?

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአሽከርካሪና ተሽከርካሪ ፍቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን ቃሊቲ አዲስ የአሽከርካሪዎች ብቃት ማረጋገጫና ፈቃድ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ጎራ በማለት ቅኝት አደረግን። ባደረግነው ምልከታ ተገልጋዮች ተራቸውን ጠብቀው የአሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ ፈቃድ መረጃቸውን እየወሰዱ ሲሄዱ ተመለከትን፡፡ ከነዚህ ተገልጋዮች መካከልም ወ/ሮ ሳራ ንጉሴ አንዷ ናቸው፡፡

ወ/ሮ ሳራ የቤተሰብ መኪና ስለነበር አልፎ አልፎ መንዳት ይለማመዱ ነበር፡፡ ነገር ግን ይህን ልምድ በስልጠና በማዳበር የሙያው ባለቤት ለመሆን በመጓጓት መሰልጠናቸውን አጫውተውናል፡፡ “የአሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ ፈቃድ ለማግኘት የንድፈ ሃሳብና የተግባር ስልጠናውን አጠናቅቄ መረጃዬን ወስጃለሁ፡፡ 15 ደቂቃ ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ነው መረጃዬን ወስጄ እየተመለስኩ ያለሁት፡፡ በስልጠና ወቅት የገጠመኝ ችግር የለም፡፡ በጥሩ ሁኔታ ነው የሰለጠንኩት። አሁን በሙሉ ልብና በጥንቃቄ ነው የማሽከረክረው” ሲሉ በፈገግታ ገልፀዋል፡፡

ፓስተር ቶማስ አልኖሬ ሌላው በማሰልጠኛው ያገኘናቸው ተገልጋይ ናቸው፡፡ “ስልጠናውን በአግባቡ ሰልጥኛለሁ፡፡ የተግባር ፈተናውን ያለ ምንም እጅ መንሻ ነው ተፈትኜ የአሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ ፈቃድ የወሰድኩት። ወደ ጽህፈት ቤቱ መረጃዬን ለመውሰድ ስመጣም ባለሙያዎች ጥሩ መስተንግዶ ነው ያደረጉልኝ፡፡ ባገኘሁት እውቀት በጥንቃቄ ለማሽከርከር እጥራለሁ፡፡ አልፎ አልፎ ከተማርኩት አንፃር አንዳንድ ሾፌሮች ጥንቃቄ ሳያደርጉ ሲያሽከረክሩ አስተውላለሁ፡፡ ‘ሙያው የሚጠይቀውን ለምን አይተገብሩም’ እላለሁ፡፡ ሁሉንም ሙያ በአግባቡ በመማርና በመሰልጠን መተግበር አለብን” ሲሉም ምክረ ሃሳባቸውን አጋርተዋል፡፡

ወጣት አዶናይ አሸናፊ በጉዳይ አስፈፃሚነት ነው እየሠራ የሚገኘው፡፡ ለስራው አጋዥ እንዲሆነው በጥሩ ሁኔታ መሰልጠኑን ይናገራል፡፡ ‘በምናሽከረክርበት ወቅት በኃላፊነት ስሜት ለራስም ሆነ ለሰው ህይወት ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል’ ሲልም ይገልፃል፡፡

ነገር ግን ይላል ወጣቱ “የተግባር ልምምዱን ለመፈተን በተዘጋጀሁበት ወቅት አሰልጣኙ የእጅ መንሻ እንድሰጥ ገፋፍቶኝ ነበር፡፡ ‘ከፍለህ ታልፋለህ ወይስ ትፈተናለህ?’ ብሎ ጠየቀኝ፡፡ ከኔ በፊት የሰለጠኑ ጓደኞቼ ተጠይቀው ሳይከፍሉ ተፈትነው ማለፋቸውን ስለነገሩኝ ‘እፈተናለሁ’ ብዬ መለስኩለት፡፡ ፈተናውንም ያለ እጅ መንሻ ተፈትኜ አልፌ አሁን የአሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ ፈቃድ መረጃዬን ወስጃለሁ፡፡ በዚህም ደስተኛ ነኝ” ብሏል፡፡

በቃሊቲ አዲስ አሽከርካሪዎች ብቃት ማረጋገጫና ፈቃድ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የአሽከርካሪዎች ብቃት ማረጋገጥና ፈቃድ አገልግሎት ዳይሬክተር አቶ ፍፁም ግርማ ለጋዜጣው ዝግጅት ክፍል በሰጡት መረጃ፣ ጽህፈት ቤቱ ወርሃ መጋቢት በ2016 ዓ.ም ተቋማዊ ሪፎርም ካደረገ በኋላ አገልግሎት አሰጣጡን በቴክኖሎጂ በተደገፈ መልኩ (ዲጂታላይዝድ) አድርጓል፡፡ ተገልጋዮች እንደመጡ የወረፋ ማስጠበቂያ ቁጥር ይዘው በሲስተም ስማቸው ከተመዘገበ በኋላ በተራቸው መሰራት አገልግሎቱን አግኝተው የሚሄዱበት አሰራር መፈጠሩን ገልፀዋል፡፡

ከዚህ አኳያ ጽህፈት ቤቱ  በዋናነት የአሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ ፈቃድ ለሚወስዱ አካላት ከአዲስ አበባ የአሽከርካሪና ተሽከርካሪ ፈቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን የሚመጣውን የሰልጣኞች መረጃ መሰረት በማድረግ የአሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ ፈቃድ መረጃ የመስጠት ስራ ያከናውናል፡፡ መረጃው የሚሰጠው ስልጠናው ከተጠናቀቀ በኋላ በቴክኖሎጂ በተደገፈ አሰራር የንድፈ ሃሳብ እና የተግባር ምዘና ከተሰጠ በኋላ ነው፡፡ በሁለቱም ምዘናዎች እያንዳንዳቸው 74 እና ከዚያ በላይ በማምጣት ያለፈ ሰልጣኝ የአሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ ፈቃድ ይሰጠዋል፡፡

በዚህ ሂደት የጽሑፍ ፈተናውን ያላለፈ ሰልጣኝ 300 ብር በመክፈል በሳምንቱ እንደገና ይፈተናል፡፡ የተግባር ፈተናውን ያላለፈ ደግሞ ያለምንም ክፍያ ሦስት ጊዜ በተግባር እንዲፈተን የሚደረግበት አሰራር መኖሩንም አቶ ፍፁም ገልፀዋል። የመንጃ ፈቃድ የማደሻ ጊዜ ያለፈባቸው ተገልጋዮች ለማደስ ሲመጡ በግላቸው መኪና አልያም በማሰልጠኛ ተቋማት መኪና የተሃድሶ የተግባር ስልጠና ወሰደው እንዲታደስላቸው የማድረግ ስራም ሌላኛው አገልግሎት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የመንጃ ፈቃድ የሚሰለጥኑ አካላት ለተግባር ልምምድ ወደ ጽህፈት ቤቱ በሚመጡበት ወቅት አልፎ አልፎ በአካባቢው በሚገኙ የግል መኪና በያዙ ህገ ወጥ ደላሎች ይጋለጣሉ፡፡ ይህም “እጅ መንሻ ካልሰጣችሁ አያሳልፏችሁም፤ እኛ በትንሽ ብር በመኪናችን እናሰልጥናችሁ፤ እናለማምዳችሁ” የሚሉ አሉ፡፡ ይህ በስራ ሂደት የሚያጋጥም ተግዳሮት መሆኑን ዳይሬክተሩ ይገልፃሉ፡፡

ከዚህ ቀደም በነበረው አሰራር በህገ ወጥ መንገድ የግል መኪና ይዘው በጽህፈት ቤቱ ግቢ የሚያለማምዱ ነበሩ፡፡ ሪፎርሙ ከተሰራ በኋላ ይህ አሰራር ተወግዷል፡፡ በአሁኑ ወቅት እነዚህን አካላት ለመከላከል ከጸጥታ አካላት ጋር በቅንጅት በመስራት ወደ ጽህፈት ቤቱ  እንዳይቀርቡ፣ ከአካባቢው እንዲርቁ የማድረግ እና ለሰልጣኞችም ግንዛቤ የመስጠት ስራ እየተሰራ ይገኛል፡፡ ሰልጣኞች በህገ ወጥ መንገድ “እናሰልጥናችሁ” የሚሉ አካላት ሲያጋጥሟቸው የመንጃ ፈቃድ የንድፈ ሃሳብም ይሁን የተግባር ስልጠና የሚሰጠው እውቅና በተሰጣቸው በአሽከርካሪ ማሰልጠኛ ተቋማት ብቻ መሆኑን በመረዳት ጥንቃቄ ማድረግና መታለል እንደሌለባቸው ነው አቶ ፍፁም ያስገነዘቡት፡፡

ሰልጣኞች በአሽከርካሪ ማሰልጠኛ ተቋማት በስልጠና ወቅት እንዲሁም ውጤታቸውን አይተው ቅሬታ ካላቸው በተገቢው መንገድ እስከ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ድረስ ቅሬታ ማቅረብ የሚችሉበት ግልፅ አሰራር ተዘርግቶ እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

ጽህፈት ቤቱ  ብቃት ያለው አሽከርካሪ ለማፍራት በሚደረገው ጥረት ሙሉ በሙሉ ከሰው ንኪኪ የፀዳ ቴክኖሎጂ በመጠቀም የፈተና አሰጣጡን የበለጠ ማዘመን፣ በመሰናክል ተግባር ልምምድ ወቅት በዲጂታላይዝድ በሴንሰር ለመጠቀም የያዘውን እቅድ ለመተግበር እንዲሁም የሚሰጠውን ቀልጣፋ አገልግሎት ለማስቀጠል በትኩረት እንደሚሰራ አቶ ፍፁም ጠቁመዋል፡፡

“ማንኛውም ህብረተሰብ በህጋዊ መንገድ መጥቶ አገልግሎቱን አግኝቶ የመሄድ መብት አለው” የሚሉት ዳይሬክተሩ ህብረተሰቡ ይህን በመረዳት ራሱን ብቁ በማድረግ፣ በኃላፊነት ስሜት፣ ህጋዊ በሆነ መንገድ ብቻ የመንጃ ፈቃድ ስልጠናውን በመውሰድ የአሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ ፈቃድ ማግኘት እንደሚችል አስታውቀዋል፡፡

የዝግጅት ክፍሉ በጽህፈት ቤቱ በመገኘት ባደረገው ቅኝት፤ የመንጃ ፈቃድ የጽሑፍና የተግባር ስልጠናውን አልፈው የአሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ ፈቃድ መረጃን ለመውሰድ የሚመጡ የህብረተሰብ ክፍሎች በጽሕፈት ቤቱ  ባለሙያዎች ያለምንም እንግልት፣ ግፊያና ትርምስ እንደ አመጣጣቸው አገልግሎቱን በፍጥነት አግኝተው መረጃቸውን ይዘው ሲመለሱ ለመመልከት ችለናል፡፡

ባለስልጣኑ ምን እየሰራ ነው?

የዝግጅት ክፍላችን ብቃት ያለው አሽከርካሪ ከማፍራት አንፃር በአዲስ አበባ የአሽከርካሪና ተሽከርካሪ ፈቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን በኩል እየተሰራ ያለውን ስራ አስመልክቶ በባለስልጣኑ የአሽከርካሪ ማሰልጠኛ ተቋማት ብቃት ማረጋገጥ ዳይሬክተር ወ/ሮ ታደለች ሁሉቃን አነጋግሯል፡፡

ወ/ሮ ታደለች እንዳብራሩት፤ የዳይሬክቶሬቱ ዋና ተግባር የአሽከርካሪ ማሰልጠኛ ተቋማትን ፍቃድ ማደስ፣ ብቃታቸውን ማረጋገጥ፤ በመመሪያ መሰረት በስነ ምግባርና በብቃት ማሰልጠናቸውን ክትትልና ድጋፍ ማድረግ፣ ጥፋት አጥፍተው ከተገኙ ፈቃዳቸውን መሰረዝ እንዲሁም ጥፋት ፈፅመው የተገኙ አሽከርካሪዎችን እንደ ጥፋት ደረጃው ማስጠንቀቂያና እርምጃ መውሰድ ይጠቀሳሉ፡፡

ከማሰልጠኛ ተቋማቱ ጋር ግንኙነቱ በቴክኖሎጂ (በኦንላይን) የተደገፈ ነው። ይህም የማሳለፍ ምጣኔን በሲስተም መቆጣጠር፣ የሰልጣኝ ምዝገባን፣ ቀጠሮ ማስያዝ፣ የንድፈ ሃሳብና የተግባር ፈተና እና ሌሎችንም በቴክኖሎጂ ተደግፎ ቁጥጥር የማድረግ ስራ ይከናወናል፡፡ በከተማዋ 137 የመደበኛ አሽከርካሪ ማሰልጠኛ ተቋማት የሚገኙ ሲሆን፤ 1 ማሰልጠኛ ተቋም ስልጠናውን በአግባቡ ባለመስጠቱ ፍቃዱ ተሰርዟል። በተጨማሪም አምስት የልዩ መንጃ ፈቃድ አሽከርካሪ (ዶዘር፤ ሎቤድ፣ . . . ) ማሰልጠኛ ተቋም የነበሩ ሲሆን፤ ስልጠናውን ከስታንዳርድ በታች በመስጠታቸው ነሐሴ 2016 ዓ.ም ፈቃዳቸው መሰረዙን ነው ወ/ሮ ታደለች የገለፁት፡፡

እነዚህ ተቋማት ብቁ መሆናቸው የሚረጋገጠው፤ ብቁ የሆነ የብቃት ማረጋገጫ (ሲኦሲ) ያለው አሰልጣኝ መኖሩ፣ የተግባር ልምምድ የሚያሰለጥኑበት መኪና ቴክኒኩ የተረጋገጠ መሆኑ እንዲሁም የንድፈ ሃሳብ ማስተማሪያ ክፍሎቹ ደረጃቸውን የጠበቁ ከሆኑ ተረጋግጦ የማሰልጠን አገልግሎት እንዲሰጡ እንደሚደረግ ነው ዳይሬክተሯ የሚያስረዱት፡፡

ለማሰልጠኛ ተቋማቱም ባለሙያ በመመደብ ድጋፍና ክትትል ይደረጋል፡፡ ይህ የሚከናወነው የቴክኒክ ክፍተት እያለ ስልጠና የሚሰጡ ካሉ መከታተልና ስልጠና መስጠት፤ ክፍተታቸውን በመፈተሽ እንዲያስተካክሉ ማድረግና ግብረ መልስ የመስጠት ስራ ይሠራል፡፡ በግብረ መልሱ መሰረት ማስተካከያ የማያደርጉ ተቋማት ካጋጠሙ እርምጃ ይወሰዳል፡፡ ከባለስልጣኑ እውቅና ውጪ ሳይመዘገቡ ማስተማር፣ በትክክል ባለማሰልጠንና ስልጣኞችን ማጉላላት ካለ እርምጃ ይወሰዳል፡፡ 

የመንጃ ፈቃድ ስልጠና የሚወስዱ የህብረተሰብ ክፍሎች ምዝገባ፣ የተግባርና የንድፈ ሃሳብ ፈተና እንዲፈተኑ ቀጠሮ በመያዝ፤ መረጃቸውን በማጠናከር ለቃሊቲ አዲስ አሽከርካሪዎች ብቃት ማረጋገጫና ፈቃድ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት በመላክ በቅንጅት እየተሰራ ነው፡፡

በሰገነት አስማማው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review