የአንካራው ስምምነት ለኢትዮጵያ ምን ያስገኝላታል?

You are currently viewing የአንካራው ስምምነት ለኢትዮጵያ ምን ያስገኝላታል?

ስምምነቱ በአፍሪካ ቀንድ ቀጣናዊ ውህደት ለመፍጠር የሚደረገውን ጥረት የሚያግዝ ነው

የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ምሁር አቶ በፈቃዱ ዳባ

ኢትዮጵያ ወደብ አልባ ሀገር መሆኗ በርካታ ኢትዮጵያውያንን ሲያስቆጭና ሲያንገበግብ የቆየ ጉዳይ ነው፡፡ ከአንድ ዓመት በፊት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በሰጡት ማብራሪያ፣ የኢትዮጵያ ህልውና ከቀይ ባህር ጋር የተሳሰረ እንደሆነ ጠቅሰው፣ የባህር በር ማግኘት “የህልውና ጉዳይ እንጂ ቅንጦት” እንዳልሆነ፣ ከኢኮኖሚ፣ ከታሪክ፣ ከህግ፣ ከመልክዓ-ምድር፣ ከህዝብ አሰፋፈርና ሌሎች አመንክዮዎች አንጻር ማግኘት የምትችልበት እድል እንዳለ አነሱ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወቅቱ ያነሱት ሀሳብ ኢትዮጵያ የባህር በር ማጣቷ ሲያንገበግባቸው የነበሩ ኢትዮጵያውያን ደስ ያሰኘ ዜና ነበር። እነሆ ከዚያን ጊዜ ወዲህ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ በኢትዮጵያና በአፍሪካ ብሎም በዓለም አቀፍ ደረጃ ጭምር አጀንዳ የሆነበት፣ ኢትዮጵያ ፍላጎቷን እውን ለማድረግ ከተለያዩ የጎረቤት አገራት ጋር እንቅስቃሴዎች ያደረገችበትና ጥያቄዋም በበጎ ታይቶ አዎንታዊ ምላሽ እያገኘ የመጣበት ደረጃ ላይ ተደርሷል፡፡

ከዲፕሎማሲው ትሩፋት መካከል በአንካራ የተደረገው የኢትዮጵያ እና የሶማሊያ ስምምነት ተጠቃሽ ነው

ባለፈው ሳምንት መጨረሻ በተርኪዬ አደራዳሪነት በአንካራ ኢትዮጵያና ሶማሊያ ልዩነቶችንና አለመግባባቶችን በመተው ለጋራ እድገትና ብልፅግና በትብብር አብረው ለመስራት፣ ኢትዮጵያ በሶማሊያ የባህር ዳርቻ አስተማማኝ፣ ደህንነቱ የተጠበቀና ዘላቂ የባህር መተላለፊያ በምታገኝበት ሁኔታ ላይ የቴክኒክ ውይይቶችን ለመጀመር ስምምነት ላይ ደርሰዋል፡፡

የባህር በር ለኢትዮጵያ ያለው አስፈላጊነት

አቶ በፈቃዱ ዳባ የፖለቲካ ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ምሁር ሲሆኑ በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ እና በኒው ጀነሬሽን ዩኒቨርሲቲ ዲፕሎማሲ አስተምረዋል፡፡ በሶማሊላንድ  ሃርጌሳ ዩኒቨርሲቲ ለበርካታ ዓመታት ሰላምና ደህንነት ጉዳዮች እያስተማሩ ይገኛሉ፡፡ ጉዳዩን አስመልክቶ  ለዝግጅት ክፍላችን በሰጡት ማብራሪያ ላይ፣ ከ120 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ያላት ሀገር ኢኮኖሚያዊ እድገቷን ለማፋጠን፣ ህልውናዋንና ደህንነቷንም ለማስከበር የባህር በር ያስፈልጋል፡፡ የባህር በር ለኢትዮጵያ የመኖር ያለመኖር፤ የትውልድ ጥያቄ ነው። ኢትዮጵያ ከ1983 ዓ.ም በኋላ ወደብ አልባ የሆነችበት ሁኔታ “ታሪካዊ ስህተት” የሚባል እንደሆነ ያነሳሉ፡፡

የፖለቲካ ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ምሁር አቶ በፈቃዱ ዳባ

የባህር በር የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊና የደህንነት ህልውና የሚበይን ጉዳይ እንደሆነ የሚናገሩት ደግሞ በዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ የውጭ ግንኙነትና ዲፕሎማሲ መምህር አበራ ሄብሶ ናቸው። ኢትዮጵያ ኢኮኖሚዋ እያደገና እየሰፋ በመምጣቱ ወደ ሀገር ውስጥና ወደ ውጭ የምትልካቸው ምርቶች መጠን በከፍተኛ ደረጃ እያደጉና በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ እየሆነች መጥታለች፡፡ በዚህም ምክንያት ለወደብ ኪራይ የምታወጣው ወጪ መጨመር የኢኮኖሚ እድገቷ ላይ ጫና እያሳደረ ይገኛል። የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለስልጣን ባለፈው ዓመት ያወጣውና በገፀ ድሩ ላይ የሚገኘው እንደሚያሳየው ኢትዮጵያ በዓመት ለወደብ ኪራይ ክፍያ እስከ 1 ነጥብ 6 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ታወጣለች፡፡

የባህር በር የሀገርን ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ ከፍ ያለ ጠቀሜታ እንዳለው የውጭ ግንኙነትና ዲፕሎማሲ መምህሩ አበራ ያነሳሉ፡፡ ኢትዮጵያ ደህንነቷን ለማስጠበቅ የሚያስፈልጋት ወታደራዊ ቁሳቁስ በነፃነትና ወታደራዊ ምስጢርን በጠበቀ መልኩ ማከናወን የማትችል ከሆነ የሀገርን ብሔራዊ ደህንነት አደጋ ላይ ይጥላል፡፡ ከዚህ አኳያ የሀገርን ደህንነት ለማስጠበቅ የባህር በር ማግኘት ወሳኝ እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡

ኢትዮጵያ ወደብ አልባ የሆነችበትን ሁኔታ በማረም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ሀገሪቱ በአፍሪካ ቀንድና በአህጉሩ ካላት የህዝብ ቁጥር፣ የኢኮኖሚ አቅም፣ ሰላምና ፀጥታን በማስጠበቅ ከምትጫወተው ሚና አኳያ በሰጥቶ መቀበል መርህ የባህር በር እንድታገኝ የወሰዱት እርምጃ የሚደገፍ እንደሆነም የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ምሁሩ በፈቃዱ ያስረዳሉ፡፡

ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት የባህር በር ልታገኝ የምትችልባቸው የተለያዩ አማራጮች አሉ፡፡ ጎረቤት አገራት ረጅም የባህር ጠረፍ፣ ሊለሙ የሚችሉና ያለ ስራ የተቀመጡ ወደቦች አሏቸው። እነዚህን መጠቀም ቢቻል አገራቱ ገቢ የሚያመነጩበት፣ ኢትዮጵያም ተጠቃሚ የምትሆንበት ዕድል ሰፊ ነው፡፡

ታሪካዊው የኢትዮ-ሶማሊያ ግንኙነት

ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ረጅም ድንበር፣ የጋራ ማንነትና ቋንቋ የሚጋሩ ወንድማማችና እህትማማች ህዝቦች ናቸው፡፡  በተለይ ሶማሊያ የእርስ በርስ ጦርነት በገባችበት ወቅት በርካታ ሶማሊያውያን ኢትዮጵያን መጠጊያና መሸሸጊያ አድርገው ይኖራሉ፡፡ መጠለያ እንዲያገኙ፣ እንዲማሩ፣ ተረጋግተው እንዲኖሩ ትልቅ ድጋፍ በማድረግ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱ ተጠናክሯል። ለምሳሌ፡- በአዲስ አበባ ቦሌ ሚካኤል አካባቢ በርካታ ሶማሊያውያን ይኖራሉ። ብዙዎችም የኢትዮጵያን ቋንቋ የሚያውቁና የሚናገሩ፣ ኢትዮጵያን እንደ ሁለተኛ ቤታቸው የሚቆጥሩ፣ በኢትዮጵያ የተለያዩ ተቋማት ተምረው ዛሬ ከፍተኛ የስልጣን ደረጃ ላይ በመድረስ ሀገራቸውን እስከ ማገልገል መድረሳቸውን በፍቃዱ ያነሳሉ፡፡

ሰላማዊው የኢትዮጵያ አካሄድና የአንካራው ስምምነት

ባለፈው ሳምንት በተርክዬ ፕሬዝዳንት ረሲፕ ጣይብ ኤርዶሃን አደራዳሪነት በተደረሰው የኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ስምምነት ሁለቱ ሀገራት ልዩነቶቻቸውን ወደ ጎን በመተው በጋራ ለመስራት ተስማምተዋል፡፡

በሁለቱ አገራት መካከል ተፈጥሮ የነበረው አለመግባባት በድርድር መፈታቱ በቀጣናው ሊከሰት የሚችለውን ስጋት ያረገበና በኢትዮጵያና ሶማሊያ መካከል ያለውን ወንድማማችነት እና እህትማማችነትን የሚያጠናክር እንደሆነ የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ምሁሩ በፍቃዱ ይገልፃሉ፡፡ ኢትዮጵያና ሶማሊያ ከፍጥጫ ይልቅ በመቀራረብ፣ ተሳስረውና ተደጋግፈው በመስራት ማደግ የሚችሉባቸው ሰፊ ዕድል አላቸው፡፡ ኢትዮጵያ ከፍተኛ የህዝብ ቁጥር ያላት ሀገር ናት፡፡ ወደ ሶማሊያ የሚፈስሱ እንደ ዋቢ ሸበሌ፣ ገናሌ፣ ዳዋ ያሉ ድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ከኢትዮጵያ የሚመነጩ ናቸው። ኢትዮጵያ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ጨምሮ ትላልቅ የሀይል መሰረተ ልማቶች በመገንባት ከምታገኘው የኤሌክትሪክ ሀይል ለሶማሊያ በማቅረብ ተጠቃሚ የምትሆንበት ዕድል አለ፡፡ የኢትዮጵያ የባህር በር ማግኘት ሁለቱንም ህዝቦች በጋራ ተጠቃሚ ያደርጋል። በአፍሪካ ቀንድም ቀጣናዊ ውህደት ለመፍጠር የሚደረገውን ጥረት ያግዛል። ከዚህ አኳያ በአንካራ የተደረሰው ስምምነት በጎ ጅምር እንደሆነ  ያነሳሉ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) በተርክዬ አንካራ የተደረሰው ስምምነት በተፈረመበት ወቅት እንደተናገሩት፣ ኢትዮጵያና ሶማሊያ ጎረቤት ብቻ ሳይሆኑ ዕጣ ፈንታቸው በደም የተሳሰረ ወንድማማችና እህትማማች ህዝቦች ናቸው፡፡ ከቋንቋና ባህል ተጋርዮሽ ባለፈ  በሺህ የሚቆጠሩ የኢትዮጵያ ወታደሮች የሶማሊያን ደህንነት ከአሸባሪዎች ለመጠበቅ በከፈሉት የደም መስዋዕትነት የተሳሰሩም ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ ቀጣናዊ ውህደትና ትብብር እንዲፈጠር እየሰራች እንደምትገኝና አስተማማኝ፣ ደህንነቱ የተጠበቀ፣ ቀጣይነት ያለውና ጎረቤት ሀገራትን  ተጠቃሚ የሚያደርግ ዘላቂ የባህር በር እንዲኖራት በሰላማዊ መንገድ እንደምትሻ ተናግረዋል፡፡

የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሐሙድ በበኩላቸው፣ የኢትዮጵያ ወታደሮች ለሶማሊያ ሰላምና መረጋጋት ለከፈሉት መስዋዕትነት እውቅና እንደሚሰጡ፣ ሁለቱ ሀገራት ከሚለያያቸው ይልቅ አንድ የሚያደርጋቸው ጉዳዮች ብዙ እንደሆኑና የህዝቦችን የጋራ ተጠቃሚነት ሰላማዊ በሆነ መንገድ ለማረጋገጥ ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸውን ግንኙነት ለማሳደግና በትብብር ለመስራት ዝግጁ እንደሆኑ ጠቁመዋል፡፡  

የውጭ ግንኙነትና ዲፕሎማሲ መምህሩ አበራ እንዲሁ ኢትዮጵያ እየሄደች ያለበት መንገድ በዘላቂነት የባህር በር የመጠቀምና በባለቤትነት ይዞ የማስተዳደር ፍላጎቷን ማሳካት የሚያስችል ነው፡፡ በአንካራው ስምምነት ሶማሊያ ኢትዮጵያ ሰላም በማስከበር የከፈለችውን የደምና አጥንት ውለታ የተገነዘበችበት፣ ደህንነቱ የተጠበቀ የባህር በር ለማመቻቸትም የፈቀደችበት፤ በጥቅሉ ሁለቱ ሀገራት አብሮ ለመስራትና ለማደግ በር የከፈተ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ላይ ጥቃት ለመሰንዘር የሞከሩ አገራትን ጭምር ተስፋ የሚያስቆርጥ ነው ይላሉ፡፡

የአንካራው ስምምነት ኢትዮጵያ የባህር በር የምታገኝበትን ዕድል ያሰፋ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከጅቡቲ ጋር ጠንካራ ግንኙነት ያላት ሲሆን ካላት ወደቦች መካከል አንዱን በባለቤትነት ይዛ እንድታስተዳደር ጥያቄ እያቀረበች እንደሆነ ያክላሉ፡፡

በአሁኑ ወቅትም ሁለቱ አገራት ከፍጥጫ ይልቅ በመመካከርና በጋራ አብረው ማደግ የሚችሉበትን ሁኔታ መቀየሳቸው ወንድማማችና

እህትማማች ለሆኑት የኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ህዝቦች ትልቅ ጠቀሜታ ይኖረዋል። ኢትዮጵያ በሰጥቶ መቀበል መርህ፣ የዓለምን ህዝብ በማሳመንና በጎ ተፅዕኖ በመፍጠር የባህር በር ለማግኘት እየሄደችበት ያለው መንገድ ውጤት እያመጣ ነው፡፡

የፖለቲካ ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ምሁሩ በፈቃዱ እንዳነሱት፣ ሶማሊያ የተለያዩ የወደብ አማራጮች አላት፡፡ ከእነዚህ ወደቦች አንዱን በሰጥቶ መቀበል መርህ ኢትዮጵያ አልምታ የምትጠቀምበት መንገድ ቢፈጠር ሁለቱ ህዝቦች አልሻባብን በመዋጋት፣ ሰላምና ልማትን በማምጣት ህዝቦቻቸው ተጠቃሚ የሚሆኑበትን እድል ያሰፋል። የዚህ ታሪካዊ ስምምነት መጎልበት በቀጣናው ሰላምና መረጋጋትንና ልማትን ለማምጣት መሰረት ይጥላል፡፡

የተባበሩት መንግስታት፣ የአፍሪካ ህብረት፣ የምስራቅ አፍሪካ በይነ መንግስታት ልማት ድርጅት (ኢጋድ)፣ የአውሮፓ ህብረት፣ እንግሊዝና አሜሪካ ባሉ ዓለም አቀፍ ተቋማትና ሀገራት የአካራው ስምምነት በበጎ መታየቱ ለኢትዮጵያ የባህር በር ፍላጎት እውቅናና ህጋዊ ድጋፍ መስጠታቸውን እንደሚያሳይም ምሁሩ ያስገነዝባሉ፡፡

የአፍሪካ ቀንድ አውሮፓና እስያን የሚያገናኝ፣ የዓለም አይን ያረፈበት ዓለም አቀፋዊ የንግድ መስመር ነው፡፡ በቀጣናው  የራሳቸው  ፍላጎት   እና ጥቅም ፍላጎት ያላቸው ሀገራት አካባቢው ሰላሙ እንዲናጋና እንዲበጠበጥ ስለማይፈልጉ ሶማሊያና ኢትዮጵያ ለደረሱበት ስምምነት ድጋፍ አሳይተዋል። የኢትዮጵያ አካሄድም ብሔራዊ ጥቅሞቻቸውን የሚያስጠብቅላቸው እንደሆነ መረዳታቸውን ያሳያል፡፡ ይህም ኢትዮጵያ በኢኮኖሚና በዲፕሎማሲ እያስመዘገበች ካለው ውጤት ጋር ተያይዞ የመጣ እንደሆነ የውጭ ግንኙነትና ዲፕሎማሲ መምህሩ አበራ ያስረዳሉ፡፡

በአፍሪካ ቀንድ ቀጣና የውጭ ሀይሎች የሚያደርጓቸው የጦር ሰፈር ግንባታ እንቅስቃሴዎች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ኢትዮጵያን ይነካል፡፡ ከዚህ አኳያ ኢትዮጵያ የማንም ፈቃድ ሳትጠይቅ ዕቃዎችን የምታስገባበትና የምታስወጣበት ሁኔታ መፍጠር የዓለም አቀፍ ህግና ልማድ የሚፈቀድ ነው። በመንግስት በኩል የሚደረገውን መደበኛ ዲፕሎማሲ እና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን በመጠቀም በጎ ተፅዕኖ በመፍጠር ፍላጎቷን እውን ማድረግ ትችላለች፡፡ በዚህ ረገድ ልምድ ያላቸው ዲፕሎማቶችንና የዳያስፖራውን አቅም በመጠቀም የኢትዮጵያ የባህር በር ማግኘት አብሮ የማደግ ዓላማ ያለው መሆኑን ማሳመን ያስፈልጋል፡፡

ኢትዮጵያ የአፍሪካ እምብርት፣ ከፍተኛ የህዝብ ቁጥር፣ ሰፊ የቆዳ ስፋትና የተፈጥሮ ሀብት ባለቤት የሆነች ትልቅ አቅም ያላት ሀገር ናት። ይህንን አቅም በማሳየት የዓለም አቀፍ ህግን ባከበረ መንገድ፣ የተባበሩት መንግስታት፣ የአፍሪካ ህብረት እና ኢጋድ የቀየሷቸውን ልምዶችና አካሄዶችን ተከትሎ መሄድ በዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ዘንድ ድጋፍ ያስገኛል። በተጀመረው ጥረት ላይም የህዝብ ለህዝብ ዲፕሎማሲን መጠቀም፣ ሁሉም ዜጋ የሀገሩ አምባሳደር እንዲሆን በማድረግ መስራት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል፡፡

የውጭ ግንኙነትና ዲፕሎማሲ መምህሩ አበራ እንደሚሉት ሶማሊያ ከኢትዮጵያ የምታገኛቸው በርካታ ጥቅሞች አሉ፡፡ ኢትዮጵያ በቀጣናው ትልቅ አቅም ያላት ሀገር ናት፡፡ ሶማሊያ ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር መስራቷ ብሔራዊ ጥቅሟን ለማስጠበቅ ያስችላታል፡፡ ጂኦፖለቲካዊ ጠቀሜታ ባለው አካባቢ የምትገኝ እንደመሆኗ ኢትዮጵያም ከሀገሪቱ ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ማጠናከሯ ከሌሎች ሀገራት ጭምር የባህር በርና ወደብ የምታገኝበትን ዕድል እንደሚያሰፋ አስረድተዋል፡፡

በስንታየሁ ምትኩ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review