የአንጀት ካንሰር ከትልቁ አንጅት አንስቶ እስከ ፊንጢጣ ድረስ ባለው የሰውነት ክፍል እንደሚከሰት የካንሰር ቀዶ ህክምና እስፔሻሊስት ሀኪም ዶክተር ሙሉጌታ ካሳሁን ይናገራሉ፡፡
ከአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ጋር ቆይታ ያደረጉት የቅዱስ ጳውሎስ ሚሌኒየም ሜዲካል ኮሌጅ የካንሰር ቀዶ ህክምና እስፔሻሊስት ሀኪም ዶክተር ሙሉጌታ ካሳሁን፤ የአንጀት ካንሰር መንስኤዎች ጥሬ ሥጋ መብላት፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አለማድረግ፣ ሲጋራ ማጨስ እና የአልኮል መጠጦችን መጠቀም ዋነኞቹ ምክንያቶች እንደሆኑም ያነሳሉ።
የአንጀት ካንሰር ህመም በወንዶችም በሴቶችም የሚከሰት ሲሆን፤ በታዳጊ ወይም በለጋ ዕድሜ በሚገኙ ህፃናትም ጭምር መከሰት መጀመሩን ዶክተር ሙሉጌታ ይናገራሉ፡፡
በተለይም የፊንጢጣ የታችኛው ክፍል ላይ የሚከሰተው ካንሰር፣ በዋናነት በወጣቶች ላይ እየተከሰተ መሆኑን ያነሱት ባለሙያው፤ በማንኛውም የዕድሜ ክልልም ሊከሰት የሚችል መሆኑ አሳሳቢ እንዳደረገው ተናግረዋል።
የአንጀት ካንሰር ምልክቶች በፊንጢጣ አከባቢ መድማት፣ የአንጀት ድርቀት፣ ተቅማጥ፣ በግራ ወይም በቀኝ ሆድ በኩል ህመም፣ አንዳንዴም በብዛት የሚደማ ከሆነ እራስ ማዞር፣ መድከም፣ የምግብ ፍላጎት መቀነስ እንደሆኑም ያብራራሉ።
የህመሙን ደረጃ በመለየትም እየደማ የሚያስቸግር ከሆነ ናሙና በመውሰድ በቀዶ ጥገና ማውጣት ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ እንደሆነም ያስገነዝባሉ።
ከቀዶ ጥገናው በኋላ በኬሞቴራፒ ተከታታይ ህክምና በመስጠት በሽታውን ማከም እንደሚቻል የገለፁት ዶክተር ሙሉጌታ፤ በቀጣይነትም እራስን ከበሽታው ለመከላከል የአካልብቃት እንቅስቃሴ ማድረግና ኮሎኖስኮፒ ምርመራ እያደረጉ እራስን መጠበቅ እንደሚገባ ምክረ ሀሳባቸውን ለግሰዋል።
በወርቅነህ አቢዮ