የአካባቢያችንን ሰላም በተሟላ መንገድ በመጠበቅ የልማት ስራዎች እንዲሳለጡ ለማድረግ ተዘጋጅተናል – ተመራቂ የሰላም አስከባሪዎች

You are currently viewing የአካባቢያችንን ሰላም በተሟላ መንገድ በመጠበቅ የልማት ስራዎች እንዲሳለጡ ለማድረግ ተዘጋጅተናል – ተመራቂ የሰላም አስከባሪዎች

AMN – ታኅሣሥ 20/2017 ዓ.ም

የአካባቢያቸውን ሰላም በተሟላ መንገድ በመጠበቅ የልማት ስራዎች እንዲሳለጡ ለማድረግ መዘጋጀታቸውን የምዕራብ ጎንደር ዞን ተመራቂ የሰላም አስከባሪ አባላት ገለፁ።

በዞኑ ከመተማ ወረዳ እንዲሁም ከገንዳ ውኃና መተማ ዮሃንስ ከተማ አስተዳደሮች ተውጣጥተው ስልጠና የተከታተሉ የሰላም አስከባሪ አባላት በገንዳ ውሃ ከተማ ማዕከል ዛሬ ተመርቀዋል።

ከተመራቂዎች መካከል አቶ ሙሀመድ ታደሰ እንደገለጹት፤ የተሰጣቸው ስልጠና የአካባቢያቸውን ሰላም በዘላቂነት ለማስጠበቅ የሚያስችል ነው።

የተግባርና የንድፈ ሃሳብ ስልጠናው ተልዕኳቸውን በብቃት ለመወጣት እንደሚያግዛቸውም ተናግረዋል።

የአካባቢያቸውን ሰላም በተሟላ መንገድ በመጠበቅ የልማት ስራዎች እንዲሳለጡ ለማድረግ መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።

ሌላኛው ተመራቂ ወጣት ደስታው ሳምቡስ በበኩሉ፤ አካባቢው ሰፊ የልማት ኮሪደርና ከፍተኛ የንግድ እንቅስቃሴ የሚካሄድበት በመሆኑ ሰላምን መጠበቅ የግድ ነው ብሏል።

በተሰጠው ስልጠና መሰረት የአካባቢውን ሰላም በማስጠበቅ ልማት እንዲፋጠን ሚናውን እንደሚወጣ ተናግሯል።

መስራትና መኖር የሚቻለው ሰላም ሲኖር ነው ያሉት ደግሞ ከተመራቂዎቹ መካከል የሆኑት አቶ አወቀ አደራጀው ናቸው።

ለዘላቂ ሰላም መስፈንና ለልማት ስራዎች መሳለጥ ሀላፊነታቸውን በአግባቡ ለመወጣት መዘጋጀታቸውን አመልክተዋል።

የዞኑ ምክትል አስተዳዳሪ አቶ አንዳርጌ ጌጡ በበኩላቸው፤ ስልጠናው ዘላቂ ሰላም ለማስፈን ያግዛል ብለዋል።

ሰላምን ለማስከበር በቁርጠኝነት መደራጀታችሁና መሰልጠናችሁ ወሳኝ ነው፤ በአካባቢው ዘላቂ ሰላም ለማስፈን በሚደረገው ጥረት ሀላፊነታችሁን እንድትወጡ ሲሉም ለተመራቂዎቹ አስገንዝበዋል።

የዞኑ አስተዳደር የህዝብ ተሳትፎ አደረጃጀት ዘርፍ አማካሪ አቶ እያሱ ይላቅ በበኩላቸው፤ የህዝቡን ሰላምና ደህንነት በመጠበቅ ነዋሪው ልማቱን እንዲያፋጥን የሰላም አስከባሪ አካላት ድርሻ የጎላ ነው ብለዋል።

በሀገር መከላከያ ሰራዊት የ504ኛ ኮር ምክትል አዛዥ ኮለኔል ቾምቤ ወርቁ በበኩላቸው፤ የሰላም አስከባሪ አካሉ የአካባቢውን ሰላም በማስከበር ሚናውን እየተወጣ መሆኑን ገልጸዋል።

ተመራቂ ሰላም አስከባሪዎች በተሰጣቸው ስልጠና መሰረት የህዝብን ሰላምና ደህንነት ማረጋገጥ እንዳለባቸው ማስገንዘባቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review