AMN – የካቲት 26/2017 ዓ.ም
የአዉሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ የጥሎ ማለፍ ጨዋታዎች ዛሬም ቀጥለዉ የሚደረጉ ሲሆን ምሽት 5 ሰአት ላይ ፒኤስጂ ሊቨርፑልን የሚያስተናግድበት ጨዋታ ይጠበቃል፡፡
በአለማችን ምርጥ ከሆነዉ እና በመድረኩ ልምድ ካለዉ ፒኤስጂ ጋር የምናደርገዉ ጨዋታ ከባድ ይሆናል ሲሉ የሊቨርፑሉ አሰልጣኝ አርን ስሎት ተናግረዋል፡፡
በሊቨርፑል በኩል በዉድድር አመቱ 16 ግቦችን በማስቆጠር የክለቡ ኮከብ ግብ አስቆጣሪ የሆነዉ ኮዲ ጋክቦ ላይሰለፍ እንደሚችል የተዘገበ ሲሆን ቡድኑን ሊጎዳዉ ይችላልም ተብሏል፡፡
ሁለቱ ክለቦች ከዚህ በፊት በተገናኙባቸዉ 2 ጨዋታዎች አንድ አንድ ግዜ ተሸናንፈዋል፡፡

ሁለቱን የጀርመን ክለቦች ባየር ሙኒክ እና ባየር ሊቨርኩሰንን በተመሳሳይ ሰአት የሚያገናኘዉ መርሀ ግብርም ትኩረትን ስቧል፡፡
ክለቦቹ በአዉሮፓ መድረክ ሲገናኙ የመጀመሪያቸዉ ሲሆን ዣቪ አሎንሶ ባየር ሊቨርኩሰንን ከያዘ ጀምሮ ከባየርሙኒክ ጋር ባደረጋቸዉ 6 ጨዋታዎች አልተሸነፈም፡፡
ባርሴሎና ከሜዳዉ ዉጭ ከቤኔፊካ ጋር ይጫወታል፡፡
ሁለቱ ክለቦች በአዉሮፓ መድረክ ለ11 ጊዜ የሚገናኙ ሲሆን ባርሴሎና ከፖርቹጋል ክለቦች ጋር ባደረጋቸዉ 10 ጨዋታዎች አልተሸነፈም፡፡
ምሽት 2፡ ከ45 ላይ ደግሞ ኢንተር ሚላን ከሜዳዉ ዉጭ ወደ ሆላንድ ተጉዞ ፌይኖርድን ይገጥማል፡፡
በአልማዝ አዳነ