የአውሮፓ ህብረት የጋራ ተነሳሽነት (ኢኒሼቲቭ) የህክምና ስፔሻላይዜሽንን በኢትዮጵያ ለማጠናከር በህብረቱ አባል ሀገራት እየተተገበረ እንደሚገኝ የጤና ሚኒስቴር ገለጸ

AMN-ኅዳር 21/2017 ዓም

የአውሮፓ ህብረት የጋራ ተነሳሽነት የህክምና ስፔሻላይዜሽንን በኢትዮጵያ ለማጠናከር በህብረቱ አባል ሀገራት እየተተገበረ እንደሚገኝ የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር አየለ ተሾመ ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ የህክምና ስፔሻላይዜሽንን ለማጠናከር በመተግበር ላይ የሚገኘው የአውሮፓ ህብረት የጋራ ተነሳሽነት ሁለተኛ ጉባኤን አካሂዷል ።

የተነሳሽነቱ (ኢኒሺዬቲቩ) ዓላማ የኢትዮጵያን የጤና አቅም መደገፍ ሲሆን፤ ይህም ወደፊት ሊከሰቱ የሚችሉ ተግዳሮቶችን የበለጠ እንዲቋቋም ማድረግ የሚያስችል መሆኑ ተመልክቷል ።

ኢኒሺዬቲቩ የፖሊሲ ውይይት የሚደረግበት እና የአውሮፓ ህብረት እና አባል ሀገራት ሁለንተናዊ የጤና ስርዓቶች ሽፋንን ለማጠናከር እንደ መሰረት አድርጎ የሚያሳይ ቁርጠኝነት ነው ተብሏል ።

ከግጭት በኋላ የጤና ተቋማትን መልሶ መገንባት እና በጤናው ዘርፍ የአቅም ግንባታ ላይ ልዩ ትኩረት በመስጠት የዘላቂ ልማት ግቦችን ለማሳካት እንደሚረዳም ዶ/ር አየለ አክለዋል።

የአውሮፓ ህብረት የጋራ ኢኒሼቲቭ የኢትዮጵያ ጤና ሚኒስቴር ቅድሚያ ከሚሰጣቸው ጉዳዮች ጋር የተጣጣሙ ፕሮጀክቶችን እንደሚተገብር የአውሮፓ ህብረት ልዑክ የኢትዮጵያ ጽህፈት ቤት አምባሳደር ሶፊ ፍሮም ኢመስበርገር ገልጸዋል።

ፕሮጀክቱ የጤና ባለሙያዎች ስፔሻሊቲ እና መካከለኛ ደረጃ የጤና ክብካቤ አቅራቢዎች የስልጠና እቅድ እና በክልሎች፣ ልዩ ባለሙያዎች እና ተቋማት ውስጥ ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ጉዳዮች ትኩረት በመስጠት እንደሚተገበርም ገልጸዋል።

ፕሮጀክቱ በ9 የዩኒቨርሲቲ ሆስፒታሎች ውስጥ አኔስቲዚዮሎጂ፣ ክሪቲካል ኬር እና የህመም ማስታገሻ፣ የድንገተኛ እና ወሳኝ እንክብካቤ መድሃኒት፣ ኦርቶፔዲክስ እና ትራማቶሎጂ፣ የማህፀን ሕክምና፣ የሕፃናት ሕክምና እና የሕፃናት ጤና፣ ሳይካትሪ፣ ራዲዮሎጂ እና ቀዶ ጥገና ስፔሻሊስት ስልጠናዎችን እንደሚተገብር ተገልጿል፡፡

በጤና ሚኒስቴር እንደ ክፍተት ተለይተው የታወቁ የሆስፒታል አስተዳደር አቅምን በማጠናከር ላይ የተመሰረተ ድጋፍ እንደሚደረግ የገለጹት ደግሞ በኢትዮጵያ የስፔን አምባሳደር ጊሌርሞ ሎፔዝ ማክሌላን ሲሆኑ፤ ለሆስፒታል ስራ አስኪያጆች እና ለሚመለከታቸው የአስተዳደር ሰራተኞች ስልጠና መሰጠቱን ተናግረዋል።

በተመሳሳይ የጣሊን አምሳደር ኦውጎስቲኖ ፓሌሲ በበኩላቸው ኢኒሺዬቲቩ ጣሊያን ከሌሎች የአውሮፓ ህብረት ሃገራት ጋር በቅርበት በመተባበር በመስራት የኢትዮጵያን የጤና ዘርፍ ለማጠናከር የምታደርገውን ድጋፍ እንድታሳድግ ይረዳል ብለዋል፡፡

በጉባኤው በ9 የህክምና ኮሌጆች እየተሰጡ የሚገኙ የስፔሻስት ስልጠናዎች ሪፖርት ቀርቦ በተሳታፊዎች ውይይት እንደተደረገበት ከጤና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review