የአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ ተሳትፎን ለማግኘት እየተደረገ ያለው ትንቅንቅ

You are currently viewing የአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ ተሳትፎን ለማግኘት እየተደረገ ያለው ትንቅንቅ

AMN-ሚያዝያ 17/2017 ዓ.ም

የ2024/25 የውድድር ዓመት የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ሊጠናቀቅ በጣት የሚቆጠሩ መርሃ-ግብሮች ብቻ ቀርተዋል፡፡

ሻምፒዮኑን የፊታችን እሁድ ይለያል ተብሎ የሚጠበቀው ሊጉ ወራጆቹንም ቀድሞ አውቋል፡፡

ሊቨርፑል በሜዳው አንፊልድ ቶትንሃም ሆትስፐርስን ሲያስተናግድ የዋንጫ አሸናፊ ለመባል አንድ ነጥብ ማግኘት በቂው ነው፡፡

ሳውዝሃምፕተን እና ሌስተር ሲቲ ቀድመው ወደ መጡበት ቻምፒየንሺፕ መውረዳቸው ተረጋገጧል፡፡

ኢፕስዊች ታውንም በፕሪምየር ሊጉ አይቆይም፡፡

ሊጉ ላይ አሁንም ድረስ አጓጊ ሆኖ የቀጠለው በቀጣይ የውድድር ዓመት የአውሮፓ ተሳታፊ የሚሆኑ ክለቦችን ለመለየት የሚደረገው ትንቅንቅ ነው፡፡

የአውሮፓ ቻምፒየንስ ላይ ለመሳተፍ አምስት ቡድኖች ለሦስት ቦታዎች ይፋለማሉ፡፡

የእንግሊዝ ክለቦች ዘንድሮ በአውሮፓ መድረክ ባስመዘገቡት ውጤት ምክንያት በቀጣይ ዓመት አምስት ክለቦችን በቀጥታ ማሳተፍ ይችላሉ፡፡

ሊቨርፑል ቀድሞ ተሳትፎውን አረጋግጧል፡፡

አርሰናልም ቢሆን ሁለተኛ ደረጃውን ለሌላ አሳልፎ ይሰጣል ተብሎ አይገመትም፡፡

ሌሎች ሦስት ቦታዎች ግን አሁንም ድረስ ክፍት ናቸው፡፡

ለዚህ ቦታ ማንችስተር ሲቲ፣ ኖቲንግሃም ፎረስት፣ ኒውካስትል ዩናይትድ፣ ቼልሲ እና አስቶንቪላ ይፋለማሉ፡፡

በመጨረሻዎቹ ስድስት ጨዋታዎች አራት አሸንፎ ሁለት አቻ የተለያየው ማንችስተር ሲቲ በወሳኙ ወቅት ወደ ጥሩ ብቃት መጥቷል፡፡

በቀጣይ ቀሪ አራት ጨዋታዎች ከወልቭስ፣ ሳውዝሃምፕተን፣ ቦርንማውዝ እና ፉልሃም ጋር ይጫወታሉ፡፡

ከወቅታዊ ብቃታቸው መነሻ እነዚህን ጨዋታዎች አሸንፈው የቻምፒየንስ ሊግ ተሳትፏአቸውን እንደሚያረጋግጡ ትልቅ ግምት ተሰጥቷቸዋል፡፡

የዘንድሮ አስገራሚው ቡድን ኖቲንግሃም ፎረስት በወሳኙ ሰዓት ነጥብ መጣል ቢጀምርም አሁንም ሰፊ ዕድል አለው፡፡

የኑኖ ስፕሪቶ ሳንቶው ቡድን ከቀሪ አምስት ጨዋታዎች በተለይ ከቼልሲ ጋር የሚያደርጉት ፍልሚያ በጉጉት ይጠበቃል፡፡

ዋና አሰልጣኙ ከህመም አገግመው የተመለሱለት ኒውካስትል ዩናይትድ ከቼልሲ እና አርሰናል ጋር የሚያደርጓቸው ጨዋታዎች ፈታኝ ሊሆኑባቸው ይችላል፡፡

የ35ኛ ሳምንት መርሃግብሩን ነገ ከኤቨርተን ጋር የሚያደርገው ቼልሲ ከሌሎች ተፎካካሪዎቹ በበለጠ ከባድ ጨዋታዎች ይጠብቁታል፡፡

የምዕራብ ለንደኑ ክለብ ከሊቨርፑል፣ ኒውካስትል ዩናይትድ፣ ማንችስተር ዩናይትድ እና ኖቲንግሃም ፎረስት ጋር የመጫወት ግዴታ አለበት፡፡

አስቶንቪላም ደግሞ የመጨረሻ ሁለት ጨዋታዎቹን ከቶትንሃም እና ማንችስተር ዩናይትድ ጋር ያከናውናል፡፡

እነዚህ ውጥረት የሚበዛባቸው ጨዋታዎች ቀሪ የሊጉ ድምቀቶች ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በሸዋንግዛው ግርማ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review