የአውሮፕላን ሞተር አዲስ መሆን ጤናማነቱን እንደማይገልፅ የምርመራ ባለሙያ ገለጹ

You are currently viewing የአውሮፕላን ሞተር አዲስ መሆን ጤናማነቱን እንደማይገልፅ የምርመራ ባለሙያ ገለጹ

AMN- ሰኔ 12/2017 ዓ.ም

የአውሮፕላን ሞተር አዲስ መሆን ጤናማነቱን አይገልፅም ሲሉ በህንድ የአውሮፕላን አደጋ ምርመራ ቢሮ ይሰሩ የነበሩ የምርመራ ባለሙያ ኪሾር ቺንታ አስታውቀዋል፡፡

ባለፈው ሳምንት የተከሰከሰው የህንድ አውሮፕላን ሞተሮች አንዱ አዲስ ሲሆን፣ ሌላኛው ደግሞ የእድሳት ጊዜው በታህሳስ 2025 እንደነበር የአየር መንገዱ ሊቀመንበር ቻንድራስከራን ገልጸዋል።

በህንድ ከሚገኝ የዜና አገልግሎት ጋር ቃለ ምልለስ ያደረጉት ሊቀመንበሩ፣ ሁለቱም ሞተሮች ንጹህ ታሪክ ያላቸው መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

የቀኙ ሞተር በፈረንጆቹ መጋቢት 2025 የተገጠመ አዲስ ሞተር እንደነበርም ጠቁመዋል፡፡

የግራው ሞተር ለመጨረሻ ጊዜ ዕድሳት የተደረገለት በፈረንጆቹ 2023 እንደነበር የገለጹት ቻንድራስከራን፣ ለቀጣይ ጥገና ታህሳስ 2025 ቀጠሮ ተይዞለት እንደነበር መናገራቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

ባለፈው ሐሙስ ወደ ለንደን ሊጓዝ የነበረው ቦይንግ 787-8 ድሪምላይነር አውሮፕላን፣ በምዕራብ ሕንድ ከሚገኘው የአህመዳባድ አውሮፕላን ማረፊያ ከተነሳ ከአንድ ደቂቃ ባነሰ ጊዜ ውስጥ ተከስክሶ በትንሹ 270 ሰዎች ሕይወታቸውን ማጣታቸው ይታወሳል።

ጥቁር ሳጥኑ እና ቅጂዎቹ ስለ አውሮፕላኑ ንጹህ መሆን በሚገባ እንደሚያስረዱ ሁሉም ባለሙያዎች እንደነገሯቸው የገለፁት ቻንድራስከራን፣ ያንን መረጃ መጠበቅ የተሻለ እንደሚሆንም ተናግረዋል፡፡

በህንድ የአውሮፕላን አደጋ ምርመራ ቢሮ ይሰሩ የነበሩት የምርመራ ባለሙያ ኪሾር ቺንታ በበኩላቸው፣ የአውሮፕላን ሞተር አዲስ መሆን ጤናማነቱን አይገልፅም ብለዋል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review