
AMN-ኅዳር 8/2017 ዓ.ም
የአየር ትራንስፖርት ዘርፍ ለግል ባለሀብቶች ምቹ እንዲሆን የተጀመረው ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የትራንስፖርትና ሎጂስቲክ ሚኒስትር ዶክተር ዓለሙ ስሜ ተናገሩ ::
የአቢሲኒያ የበረራ አገልግሎትና አቪዬሽን አካዳሚ ለ8ኛ ጊዜ ያሠለጠናቸውን 47 ፓይለቶች አስመርቋል፡፡
ከተመራቂዎቹ መካከል 25 የንግድ አውሮፕላን አብራሪዎች ሲሆኑ፣ 22 ደግሞ የግል አውሮፕላን አብራሪዎች መሆናቸው ተገልጿል፡፡
በምረቃ መርሐግብሩ ው ላይ የተገኙት ትራንስፖርት እና ሎጂስቲክ ሚኒስትር ዶክተር ዓለሙ ስሜ ፣ ኢትዮጵያ ለበርካታ ዓመታት በአየር ትራንስፖርት በዓለም ላይ ቀዳሚ ሀገር ሆና ቆይታለች ብለዋል ::
በዚህ ዘርፍ የአቢሲኒያ የበረራ አገልግሎትና አቪዬሽን እያደረገ ያለዉ ተሳትፎ የሀገርን ኢኮኖሚ ለማሳደግ እና የሀገሪቱን የትራንስፖርት ዘርፍ ለማስፋፋት ትልቅ ድርሻ እንዳለዉም ተናግረዋል።
አቢሲኒያ የበረራ አገልግሎትና አቪዬሽን አካዳሚ የአቪዬሽን ባለሙያዎችን እጥረት ለመቅረፍ እያደረገ ያለዉ ጥረት የሚያስመስግን ተግባር መሆኑንም ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡
ዘርፉ ለግል ባለሀብቶች ምቹ እንዲሆን ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አስፈላጊዉን ድጋፍ ያደርጋልም ብለዋል።
የአቢሲኒያ የበረራ አገልግሎትና አቪዬሽን አካዳሚ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ካፒቴን ሰለሞን ግዛው፣ አቢሲኒያ የበረራ አገልግሎት ለአገሪቱ ኢኮኖሚ ዕድገት የበኩሉን አስተዋጽኦ ሲያደርግ መቆየቱን ተናግረዉ የአገር መሪዎችን ጨምሮ ለተለያዩ ዜጎች የአየር ትራንስፖርት አገልግሎት ሲሰጥ መቆየቱን ገልጸዋል ፡፡
በተለይ ተቋሙ ለበርካታ ዜጎች የአዉሮፕላን አምቡላንስ አገልግሎት መስጠቱንም ተናግረዋል ::
አቢሲኒያ የበረራ አገልግሎትና አቪዬሽን ከተመሰረተ ጀምሮ ከ13 ሃገራት የተዉጣጡ ከ2 መቶ ሀምሳ በላይ ፓይለቶችን አሠልጥኖ ማስመረቁንም ካፒቴን ሰለሞን ግዛው ገልፀዋል ፡፡
በ1992 ዓ.ም የተመሠረተው አቢሲኒያ የበረራ አገልግሎት ቀዳሚ የግል አየር መንገድ መሆኑ ተገልጿል ::
በቴዎድሮስ ይሳ