በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የሚከሰተው የሙቀት መጠን በሴቶች ላይ በካንሰር የመያዝ ዕድልን ከፍ ሊያደርግ እንደሚችል አንድ አዲስ ጥናት አመላክቷል፡፡
ፍሮንቲየርስ ኢን ፐብሊክ ሄልዝ በተባለው መጽሔት ላይ በወጣው አንድ የጥናት ውጤት ፤ በመካከለኛው ምሥራቅና በሰሜን አፍሪካ እየጨመረ የመጣው ሙቀት በጡት እና በማህፀን ጫፍ ካንሰር የመያዝ ዕድል እንዲጨምር ማድረጉን ገልጿል፡፡
ተመራማሪዎች እንደገለጹት ፤ በእያንዳንዱ ዲግሪ ሴልሲየስ የሙቀት መጨመር ሳብያ ሴቶች በካንሰር የመያዝ እና የመሞት ዕድላቸው ይጨምራል፡፡
የምርምሩ መሪ ዋፋ አቡ ኤል ኬይር ማታሪያ እንደገለጹት፤የሙቀት መጠን በጨመረ ቁጥር በተለይም የማህፀን እና የጡት ካንሰር ሞት ይጨምራል፡፡
ተመራማሪዎቹ በመካከለኛው ምስራቅ እና በሰሜን አፍሪካ ባሉ 17 ሀገራት ጥናት ያደረጉ ሲሆን እነዚህ አገራት በአሁኑ ወቅት ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያይዞ ከፍተኛ የሆነ የሙቀት ጭማሪ እያጋጠማቸው መሆኑን ጠቁመዋል።
“ሴቶች በተለይም በእርግዝና ወቅት ከአየር ንብረት ጋር በተያያዘ ለሚደርሱ የጤና ችግሮች ይበልጥ የተጋለጡ ናቸው” ሲሉ ከፍተኛ ተመራማሪ የሆኑት ሱንግሶ ቹን ተናግረዋል።
ተመራማሪዎች የእያንዳንዱን አገር የሙቀት መጠን እ.ኤ.አ ከ 1998 እስከ 2019 ድረስ ካለው የካንሰር ስታቲስቲክስ ጋር በማነጻጸር የሙቀት መጨመር በካንሰር ህመም እና ሞት መጨመር ጋር የተያያዘ መሆኑን ደርሰንበታል ብለዋል፡፡
በዚህ በካንሰር ህመምና ሞት ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸው ሀገራት ኳታር፣ ባህሬን፣ ጆርዳን፣ ሳዑዲ አረቢያ፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ እና ሶሪያ ናቸው።
ከፍተኛ የሙቀት መጠን ለካንሰር የሚያጋልጥ ቢሆንም እንደ አየር ብክለት ያሉ ሌሎች ችግሮች የካንሰር ስርጭትን ሊያባብሱ እንደሚችሉ ተመራማሪዎች አመልክተዋል።
ተመራማሪዎቹ የሙቀት መጨመር በካንሰር የመያዝን አጋጣሚ እንዴት ሊጨምር እንደሚችል ተጨማሪ ምርምር ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል ።
በመሆኑም ሀገራት ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር የተያያዙ አደጋዎችን ግምት ውስጥ ሊያስገቡ እንደሚገባም ነው የገለጹት፡፡
የካንሰር ምርመራ ፕሮግራሞችን ማሻሻል እና በአየር ንብረት የሚደርሰውን ጉዳት መቋቋም የሚችል የጤና ሥርዓት ማዳበር እንደሚያስፈልግም መጠቆማቸውን ዩ ፒ አይ አስነብቧል፡፡