የአየር ንብረት ለውጥ አደጋ የተፈናቃዮችን ቁጥር 120 ሚሊየን አድርሷል- ተመድ

You are currently viewing የአየር ንብረት ለውጥ አደጋ የተፈናቃዮችን ቁጥር 120 ሚሊየን አድርሷል- ተመድ

AMN- ህዳር 3/2017 ዓ.ም

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ አደጋ የተፈናቃዮችን ቁጥር በእጥፍ በመጨመር 120 ሚሊየን ማድረሱን አስታውቋል፡፡

በአንጻሩ በአዘርባጃን እየተካሄደ በሚገኘው የአየር ንብረት ለውጥ (ኮፕ 29) ጉባኤ ላይ አሜሪካና ቻይናን የመሰሉ ሀያላን ሀገራት አለመሳተፋቸው አነጋጋሪ ሆኗል፡፡

በዓለም ዙሪያ ከቀየአቸው ተፈናቅለው ከሚገኙ ሰዎች መካከል 75 በመቶ የሚሆኑት በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ ተጎጂ በሆኑ ሀገራት ውስጥ የሚኖሩ መሆኑን በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኛች ኤጀንሲ ገልጿል፡፡

ባለፉት 10 ዓመታት በግጭት ምክንያት በዓለም ዙሪያ ከተፈናቀሉ 120 ሚሊየን ሰዎች መካከል 90 ሚሊየን ተፈናቃዮች በከፍተኛ ሁኔታ ለአየር ንብረት ለውጥ አደጋ በተጋለጡ ሀገራት የሚኖሩ መሆናቸውን የኤጀንሲው ሪፖርት ያመላክታል፡፡

ከአጠቃላይ ተፈናቃዮች ግማሽ ያህሉ ደግሞ በሁለቱም ማለትም በግጭትና በአየር ንብረት ለውጥ ችግር ውስጥ በሚገኙ እንደ ሶማሊያ፣ ሱዳን፣ ማይናማርና ሶሪያ ባሉ ሀገራት ውስጥ ይኖራሉ፡፡

በመንግስታቱ ድርጅት የስደተኞች ጉዳይ ኮሚሽነር ፊሊፖ ግራንዲ የአየር ንብረት ለውጥ አደጋ ቀድሞም በተለያዩ ምክንያቶች የሚፈናቀሉ ዜጎችን ቁጥር በመጨመር ረገድ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል ብለዋል፡፡

700 ሺ ሱዳናዊያን በሀገራቸው ያለውን ጦርነት በመሸሽ ወደ ጎረቤት ሀገር ቻድ መሰደዳቸውም ነው የተገለጸው፡፡

ቻድ ለበርካታ ዓመታት ስደተኞችን ተቀብላ ብታስጠልልም ከፍተኛ የአየር ንብረት ችግር ያለባት መሆኑ ይነገራል፡፡

በሱዳን ያሉትም ቢሆን በጎርፍና በመሰል ቀውስ ሳቢያ በተደጋጋሚ ለመፈናቀል እየተዳረጉ ይገኛል ተብሏል፡፡

በባንግላዲሽ ያሉ 70 በመቶ የሚሆኑ የማይናማር ተፈናቃዮች ደግሞ ከባድ መጠን ያለው ነፋስ በቀላቀለ ዝናብ እና ጎርፍ እንደሚሰቃዩ የተመድ ሪፖርት አመልክቷል፡፡

ቀደም ሲል በስደት ደቡብ ሱዳን የኖረው እና አሁን ላይ የማህበረሰብ አንቂ የሆነው ግሬስ ዶሮንግ ” የአየር ንብረት ለውጥ በስደተኞች ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት በአይናችን ተመልክተናል” ይላል፡፡

ውሳኔ ሰጪ አካላት የስደተኞችን ድምጽ መስማት ከቻሉ የአየር ንብረት ለውጥ እያደረሰ ያለውን የከፋ ጉዳት እንደሚገነዘቡ ተስፋ አለኝ ያለው ግሬስ ዶሮንግ፤ እኛም የመፍትሔው አካል መሆን እንችላለን ሲል ይናገራል፡፡

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ይህን መረጃ ይፋ ያደረገው በአዘርባጃን ባኩ ከተማ እየተካሄደ በሚገኘው የአየር ንብረት ለውጥ (ኮፕ 29) ጉባኤ ላይ ነው፡፡

በትናንትናው ዕለት በተጀመረው የኮፕ 29 ጉባኤ ላይ እየተገባደደ የሚገኘው የፈረንጆቹ 2024 ከፍተኛ መጠን ያለው ሙቀት ማስመዝገቡ ተመላክቷል፡፡

በመሆኑም ቀደም ሲል የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል በየዓመቱ ይደረግ የነበረው የ100 ቢሊየን ዶላር ድጋፍ ሊጨምር እንደሚገባ ጉባኤው አጽንኦት ሰጥቷል፡፡

በጉባኤው ላይ ከ200 ሀገራት የተውጣጡ ባለድርሻዎች የአየር ንብረት ለውጥን በተመለከቱ ጉዳዮች ላይ እየተሳተፉ ቢሆንም አሜሪካ፣ ቻይና፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመንና ህንድ የመሰሉ ተጽዕኖ ፈጣሪ ሀገራት ተሳታፊ ሳይልኩ መቅረታቸው አነጋጋሪ ሆኗል፡፡

እነዚህ ለካርበን ልቀት ከፍተኛ ደርሻ የሚያበረክቱ ትላላቅ ሀገራት ከጉባኤው መቅረታቸው በተሳታፊ ልዑካኖችና አክቲቪስቶች ዘንድ ሀገራቱ ለአየር ንብረት ለውጥ ዳተኛ ናቸው አስብሏል፡፡

በመሆኑም የእነዚህ ሀገራት ተሳትፎ ቢኖርም ባይኖርም ለአየር ንብረት ለውጥ የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባው አብዛኞቹ ሀገራት መከራከሪያ ያቀርባሉ፡፡

በጉባኤው እየተሳተፉ የሚገኙት ብዛት ያላቸው የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች ሲሆኑ፤ ለአየር ንብረት ለውጥ ካላቸው ተጋላጭነት አንጻር የካርበን ልቀትን ለመቀነስ የሚያስችል የፋይናንስ አቅም መፍጠር ላይ ጠንካራ ሀሳብ መሰንዘርና እና ዓለም አቀፍ ትብብር ማጠናከር ላይ ብዙ መሥራት እንደሚተበቅባቸው ይነገራል፡፡

በማሬ ቃጦ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review