የአየር ወለድ ትምህርት ቤት የልዩ ሀይል ፀረ-ሽብር አባላትን በአየር ወለድነት አሰልጥኖ አስመረቀ

You are currently viewing የአየር ወለድ ትምህርት ቤት የልዩ ሀይል ፀረ-ሽብር አባላትን በአየር ወለድነት አሰልጥኖ አስመረቀ

AMN-ጥር 22/2017 ዓ.ም

በኮማንዶ እና አየር ወለድ ዕዝ የአየር ወለድ ትምህርት ቤት የልዩ ሀይል ፀረ-ሽብር ሠልጣኞችን በአየር ወለድነት አሰልጥኖ አስመርቋል።

የኮማዶና አየር ወለድ ዕዝ አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ሹማ አብደታ በምረቃ ፕሮግራሙ ላይ በመገኘት ለተመራቂ የልዩ ሀይል ፀረ-ሽብር አባላት የአየር ወለድ ልዩ ምልክት የሆነውን የደረት ክንፍ አልብሰዋል።

የአየር ወለድ ስልጠና የወሰዱት የክፍሉ አባላት ቀደም ብለው እጅግ ፈታኝና ውስብስብ የሆነ የልዩ ሀይል ፀረ- ሽብር ስልጠና መውሰዳቸውን ሌተናል ጄኔራል ሹማ ተናግረዋል፡፡

የልዩ ሀይል ፀረ-ሽብር አባላት በግልም ሆነ በቡድን የሚሰጣቸውን ውስብስብና ልዩ ግዳጅ ለመወጣት የሚያስችላቸው አቅም እንዲኖራቸው ተደርገው በላቀ ደረጃ መሰልጠናቸውን የገለፁት ሌተናል ጄኔራል ሹማ አብደታ፣ ተመራቂዎችም የሀገሪቷ ፈጣን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት የዜጎቿን ህይወት የመቀየር ልማታዊ ጉዞ እንዳይደናቀፍ የተዘጋጁበትን ልዩ ግዳጅ በፍፁም ዲሲፕሊንና ፅናት ለመወጣት ዝግጁ መሆን እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

የአየር ወለድ ትምህርት ቤት በዚሁ ደረጃ የሚጠበቅበትን ተልዕኮ በብቃት እየተወጣ የሚገኝ በመሆኑ ለተገኘው ውጤት ያለእረፍት ለተጉት አሰልጣኞች ምስጋና አቅርበዋል፡፡

የኮማንዶና አየር ወለድ ማሰልጠኛ ማዕከል አዛዥ ኮሎኔል ቦጃ አጋ በበኩላቸው፣ የአየር ወለድ ትምህርት ቤት በማዕከሉ ስር ከሚገኙ አራት ትምህርት ቤቶች መካከል አንዱ መሆኑን በመግለፅ ትምህርት ቤቱም ራሱን በማብቃት ተቋሙ በሀገር ላይ በየትኛውም ወቅት እና ቦታ የሚቃጣን ጥቃት ለመመከት ለልዩ ግዳጅ የሚፈልገውን የሰው ሀይል በላቀ ቴክኖሎጂ እያሰለጠነ እና እያበቃ የሚገኝ ሥለመሆኑ አስገንዝበዋል፡፡

የስልጠናውን ሪፖርት ያቀረቡት የአየር ወለድ ትምህርት ቤት አዛዥ ሌተናል ኮሎኔል ፀጋዬ ካሱ፣ ትምህርት ቤቱ ተመራቂ የልዩ ሀይል ፀረ-ሽብር አባላትን በልዩ ሁኔታ በጥራት በማሰልጠን የሚፈለገውን አቅም እንዲገነቡ ማድረጉን ገልፀው ለስልጠናው ስኬት የአሰልጣኙ ሀገራዊ ፍቅርና አንድነት የጎላ አስተዋፅኦ ነበረው ማለታቸውን ከመከላከያ ሰራዊት የማህበራዊ ትስስር ገጽ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review