የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር አዋጅ ተረጂነትን በመሻገር የሀገርን ክብርና ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ በመሳሪያነት እንደሚያገለግል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ተናገሩ

You are currently viewing የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር አዋጅ ተረጂነትን በመሻገር የሀገርን ክብርና ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ በመሳሪያነት እንደሚያገለግል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ተናገሩ

AMN ግንቦት 28/2017 ዓ.ም

የኢትዮጵያ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ረቂቅ አዋጅ የተረጂነት አስተሳሰብን በመሻገር የተሟላ ሀገራዊ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ለሚደረገው ጥረት ሁነኛ መሳሪያ መሆኑን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ገለጹ።

ምክር ቤቱ በ34ኛ መደበኛ ስብሰባው የኢትዮጵያ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ረቂቅ አዋጅን በአዋጅ ቁጥር 1386/2017 ዓ.ም አፅድቋል፡፡

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ፈቲህ ማህዲ(ዶ/ር)፥ የኢትዮጵያ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ረቂቅ አዋጅ የዝግጅት ሂደትን አስመልክቶ ለምክር ቤቱ ሪፖርትና የውሳኔ ሃሳብ አቅርበዋል፡፡

የአደጋ ሥጋት አመራር የውሳኔ ሃሳብ ረቂቅ አዋጅ ከተረጂነት አስተሳሰብ በመላቀቅ ለአደጋ ሥጋት በሀገር አቅም ምላሽ ለመስጠት የሚረዳ ጠንካራ ሃሳብ የያዘ ነው ብለዋል።

በተጨማሪም አዋጁ ያልተማከለ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ሥርዓት በመዘርጋት በየደረጃው የሚገኙ የፌደራልና የክልል መንግስታት ተግባርና ኃላፊነታቸውን በአግባቡ የሚወጡበትን ድንጋጌ እንደያዘ ገልጸዋል።

የአደጋ ሥጋት ቅበላ ስራዎችን ከዘላቂ የልማት ዕቅዶችና መርሃ ግብሮች ጋር በማስተሳሰር የሰብዓዊ ድጋፍ ምላሽ አሰጣጥ መርሆችን የተከተለ እንዲሆን የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህም ከአደጋ በፊት፤ በአደጋ ጊዜና በድህረ አደጋ ወቅት የቅድመ መከላከልና መልሶ ማቋቋም ተግባራትን በውጤታማነት ማከናወን የሚያስችል አደረጃጀት እንደሚፈጥር አስረድተዋል።

በረቂቅ አዋጁ የዝግጅት ሂደት የፌደራል ስርዓትን ከሚከተሉ ዘጠኝ ሀገራት ልምድና ተሞክሮ በመውሰድ የተሻለ ግብዓት የታከለበት መሆኑንም አስረድተዋል።

በዚህ መነሻነት የምክር ቤት አባላቱ ረቂቅ አዋጁን እንዲያጸድቁት በውሳኔ ሃሳባቸው አቅርበዋል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት፥ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር አዋጅ ተረጂነትን በመሻገር የተሟላ ሀገራዊ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ለሚደረገው ጥረት ሁነኛ መሳሪያ በመሆን ያገለግላል ብለዋል።

አዋጁ ከተረጂነትና ከጠባቂነት አስተሳሰብ የሚያላቅቅ፣ ሉዓላዊነትን ማስጠበቅ የሚያስችልና ነባር የመረዳዳት እሴትን የሚያጎለብት መሆኑንም ገልጸዋል።

የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር አዋጅ ለአደጋ የተጋለጡ ሰዎችን በሀገር አቅም ለመደገፍ ከደመወዝተኛው ላይ በየወሩ ገንዘብ ለመሰብሰብ ተቀምጦ የነበረው አንቀጽ እንዲሰረዝ መደረጉን በበጎ አንስተዋል።

በቀጣይ ከህብረተሰቡ የሚሰበሰቡ ገቢዎች ሕግ፣ ደንብ እና መመሪያን በተከተለ አግባብ ተጠናክረው እንዲቀጥሉ የምክር ቤት አባላት ማሳሰባቸዉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በመጨረሻም ምክር ቤቱ በረቂቅ አዋጁ ላይ ከተወያየ በኋላ የኢትዮዽያ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ረቂቅ አዋጅን በአዋጅ ቁጥር 1386/2017 ዓ.ም በሙሉ ድምፅ አፅድቋል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review