የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መዲናዋን ጽዱ፣ ውብና አረንጓዴ ለማድረግ እያከናወነ ያለውን ውጤታማ ስራ አጠናክሮ ይቀጥላል-ኢንጅነር ወንድሙ ሴታ

You are currently viewing የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መዲናዋን ጽዱ፣ ውብና አረንጓዴ ለማድረግ እያከናወነ ያለውን ውጤታማ ስራ አጠናክሮ ይቀጥላል-ኢንጅነር ወንድሙ ሴታ

AMN-የካቲት 10/2017 ዓ.ም

በምክትል ከንቲባ ማእረግ የአዲስ አበባ ከተማ ዋና ስራ አስኪያጅ ኢንጅነር ወንድሙ ሴታ በጃፓን አለም አቀፍ ትብብር ኤጀንሲ (ጃይካ) በተዘጋጀ የጽዱ ከተሞች ኢንሼቲቭ የአካባቢ ጥበቃ አስተዳደር ጉባኤ ላይ በመሳተፍ ላይ ናቸው።

በጃፓን ዮካሃማ ከተማ እየተካሄደ ባለው በዚህ መድረክ ላይ አዲስ አበባን ጨምሮ የ7ት የአፍሪካ አገራት ከተሞች ማለትም የሉሳካ፣ ናይሮቢ፣ ቱኒዝያ አልጀሪያ፣ አቢጃን እና ካርቱም ከተሞች ከፍተኛ አመራሮች እየተሳተፉ መሆኑ ተገልጿል፡፡

የእውቀት፣ የምርጥ ተሞክሮ እና ልምድ ልውውጦች ፣ በደረቅ ቆሻሻ አስተዳደር ፣የብክለት ቁጥጥር እና ዘላቂ የከተማ ልማት ርእሰ ጉዳዮች ላይ ውይይት እየተካሄደም ይገኛል።

በመድረኩ ላይ መዲናችን አዲስ አበባን በመወከል የተገኙት ኢንጅነር ወንድሙ ሴታ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መዲናዋን ጽዱ፣ ውብና አረንጓዴ ለማድረግ እያከናወነ ያለው ውጤታማ ስራዎችን ለማጠናከር ያለውን ቁርጠኝነት አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልፀዋል፡፡

መዲናዋ የአለምዓቀፍ ምርጥ ልምዶችንም በመቀመር እያስመዘገበችው ያለውን አብነታዊ እና ስኬታማ ተግባር ለሌሎች የአህጉሩ ከተሞች ለማካፈል ይህ መድረክ ወርቃማ እድል የፈጠረ ነው ሲሉ አስገንዝበዋል።

ኢንጅነር ወንድሙ አክለውም፣ በርካታ የመስኩ ኤክስፐርቶች እየተሳተፉበት ባለው በዚህ መድረክ ለአዲስ አበባ ከተማ ጠንካራ የአካባቢ ጥበቃ ስርዓትን ለማጠናከር እና ዘላቂነቱን በማረጋገጥ ረገድ ተሻጋሪ እይታን የሚጨምሩ ጠንካራ ትስስሮችን ለመፍጠርና ከዚሁ የሚገኘውን ልምድና ተሞክሮ ለቀጣይ ስራ ለማዋል ጠቃሚ ግብአት የሚገኝበት መድረክ መሆኑንም መናገራቸውን ከአዲስ አበባ ዋና ስራ አስኪያጅ ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review