የአዲስ አበባ ኮሪደር ልማት ለከተማው አዲስና ውብ ገፅታ ከማላበስ በተጨማሪ ለሴቶችና ለወጣቶች፣ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ እና ሰው ተኮር ነው ሲሉ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የማኔጅመንት አባላትና ስራ አስፈፃሚዎች ገለጹ፡፡
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የማኔጅመንት አባላት፣ ስራ አስፈፃሚዎች በአሁኑ ወቅት በመልሶ ግንባታ ውስጥ ካሉ ስምንት ዐበይት ኮረደሮች አንዱ የሆነውንና በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በይፋ የተመረቀውን የካዛንቺስ አካባቢ ጨምሮ ሌሎች በመጀመሪያው ምዕራፍ የተከናወኑ የአዲስ አበባ ኮሪደር ልማት ስራዎችን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ቀደም ሲል ይገኝበት የነበረውና በአንድ ወቅት ከተዘነጉ የማዕከላዊ አዲስ አበባ ስፍራዎች አንዱ የሆነው ካዛንቺስን ጨምሮ አካታች እና ተደራሽነቱ የተስፋፋ ሕዝባዊ ስፍራ እንዲሆን በአዲስ ምናብ ተቃኝቶ በዚህ መልክ ማየታቸው ለከተማው አዲስና ውብ ገፅታ ያላበሱ ሰው ተኮር ስራዎች ናቸዉ ሲሉ መግለፃቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመለክታል።