የስኮትላንዱ እግር ኳስ ክለብ ሬንጀርስ ደጋፊ የሆነው የአምስት ዓመቱ ሌይተን ስቲል የአዕምሮ ውስንነት ያለበት፣ ማየት የተሳነውና በጤና ችግሮች ምክንያት ዕድሜውን ሙሉ በሆስፒታል ያሳለፈ አዳጊ ነው፡፡ ሕፃን ሌይተን ከሆስፒታል ሕክምናውን ጨርሶ ሲወጣ የሬንጀርስ ተጫዋቾች አጃቢ ሆኖ ወደ ሜዳ መግባት እንደሚፈልግ ለቤተሰቦቹ ደጋግሞ ይናገር ነበር ይላል ግላስኮ ላይቭ የተሰኘው ድረ ገጽ ያስነበበው ጽሑፍ፡፡ ሲያድግም እግር ኳስ ተጫዋች መሆን እንደሚፈልግ ድረ ገጹ አስነብቧል፡፡
ታዲያ አንድ ቀን የአዳጊው ሌይተን ህልም እውን ሆነና ከህክምናው ሲመለስ የሚወደው እግር ኳስ ክለብ ሬንጀርስ ጨዋታውን ሲያከናውን በዊልቸር ታግዞ ተጫዋቾችን በማጀብ ሜዳ ውስጥ እንዲገባ ተደርጓል። ሕፃኑ ሌይተን ከተጫዋቾች ጋር ወደ ሜዳ ሲገባም የነበረውን የደስታ ስሜት ሊገልጸው ከሚችለው በላይ ደስታ እንደፈጠረለት ወላጅ አባቱ ከድረ ገጹ ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል፡፡
በተለያየ አጋጣሚ ተጫዋቾች ለጨዋታ ወደ ሜዳ ሲገቡ ልዩ ልዩ አጃቢዎች እንደነበራቸው ታሪክ ያስረዳል። ከተጫዋቾች ጋር እጅ ለእጅ ተያይዘው ወደ ሜዳ የሚገቡ ሕፃናትም የተጫዋቾች አጃቢ (Child Mascot) ይባላሉ። በዘመናዊ እግር ኳስ እየተለመደ የመጣው ሕፃናት ከተጫዋቾች ጋር እጅ ለእጅ ተያይዘው ወደ ሜዳ የሚገቡበት ሁነት አሁን ላይ ግዴታ እስከመሆን ደርሷል፡፡
በተለይም ለተለያየ ህመም የተጋለጡ አዳጊዎችና ህጻናት የዕድሉ ተጠቃሚ እንዲሆኑ እየተደረገ ይገኛል። ህጻናትን በዚህ መልኩ ይዞ ወደ ሜዳ መግባት መች ተጀመረ? ዓላማውስ ምንድነው? የሚሉና መሰል ጉዳዮችን ደግሞ በዚህ ጽሑፍ እንቃኛለን፡፡ በእርግጥ ይህ ሰፋ ያለ ዓላማ ያለው አዳጊዎች ወደ መጫዎቻ ሜዳ ይዞ የመግባት ተግባር በትክክል መች እንደተጀመረ ቁርጥ ያለው ቀን ባይታወቅም የተለያዩ ጊዜያት ግን ይጠቀሳሉ፡፡
በዘጋርዲያን መረጃ መሰረት አዳጊዎችን ወደ ሜዳ ይዞ መግባት እ.ኤ.አ በ1970ዎቹ በብራዚል በአትሌቲኮ ሚኒሮ እና በአሜሪካ ሚኒሮ እግር ኳስ ክለቦች መካከል በተደረገው ጨዋታ ለመጀመሪያ ጊዜ እንደተጀመረ ያስረዳል፡፡ የአዳጊ ቤተሰቦችን ጨምሮ ሌሎች ደጋፊዎች ወደ ሜዳ እንዲመጡ እና ጨዋታውን እንዲከታተሉ ታስቦ በወቅቱ እንደተጀመረ ታሪክ ያሳያል፡፡ ለእያንዳንዱ ቡድን አንድ አንድ አዳጊ መታየት የጀመረውና ልጆች ከእግር ኳስ ተጫዋቾች ጋር በተደጋጋሚ በመጫወቻ ሜዳዎች መታየት የጀመሩት እ.ኤ.አ ከ1990ዎቹ ጀምሮ ነበር የሚሉም አልጠፉም፡፡
እ.ኤ.አ ከ2000 ወዲህ ደግሞ ለሕጻናት ደስታን የሚያጎናጽፈው ይህ መልካም ድርጊት የተለየ ትርጉም እና ትኩረት እየተሰጠው ይገኛል። የፈረንጆቹ የ2000 የአውሮፓ ዋንጫ ውድድር ደግሞ የቡድኑ ተጫዋቾች ክንድ እርስ በእርስ ተያይዘው የሚገቡበትን የቀድሞ ልምምድ በመተካት የተጫዋቾች አጃቢዎች ከእያንዳንዱ እግር ኳስ ተጫዋች ጋር ከታዩባቸው የመጀመሪያ ዋና ዝግጅቶች አንዱ ነበር። አብዛኛውን ጊዜ ልጆቹ ከ6 እስከ 18 ዓመት እድሜ ያላቸው ሲሆን፣ እነዚህ ልጆች የሚመረጡት ደግሞ ትንንሽ ሊግ ሲጫወቱ እና ድንቅ ስራዎችን ሲያከናውኑ ነው።
አዳጊዎች ከተጫዋቾች ጋር ወደ መጫወቻ ሜዳ የሚገቡባቸው የተለያዩ ምክንያቶች አሉ። እነዚህም ለክለቦች የገቢ ምንጭ፣ የህጻናትን መብት ዘመቻ ማስተዋወቅ፣ ህጻናት ህልማቸውን እንዲያሳኩ ዕድል መስጠት እና ተጫዋቾቹን ህጻናት እንደሚመለከቷቸውና ትውልዱን ለማነሳሳት ይጠቀሙበታል። አዳጊዎቹ ተጫዋቾችን ከማገዝ በተጨማሪ ባንዲራ መያዝ፣ የቡድን አባላትን መርዳት እና እርስ በእርስ ግጥሚያ መጫወት የመሳሰሉ ተግባራት አሏቸው። በሌላም በኩል ሕዝባዊነትን ያጎለብታል፤ ለቤተሰብ ተስማሚ የሆነ ድባብ እና የማኅበረሰብ ተሳትፎን ለማሳደግም ይጠቅማል።
አዳጊዎች በእግር ኳስ ስፖርት ከሚያደንቋቸው ከስፖርቱ ሰዎች ጋር ልዩ ጊዜ እንዲያሳልፉ፣ ልጆች የተሻለ ህይወት እና ትምህርት እንዲያገኙ ግንዛቤ ለመፍጠር እንደዚሁም ከተጫዋቾች አጠገብ ሕፃናት ካሉ ደጋፊዎች አደጋ የመፍጠር ዕድላቸው አነስተኛ በመሆኑ ዘርፈ ብዙ ጥቅም እንዳለው የዘአትሌቲክስ መረጃ በጉዳዩ ላይ ያሰፈረው ጽሑፍ ያክላል።
ጃፓን እና ደቡብ ኮሪያ በጋራ ባዘጋጁት በ2002ቱ (እ.ኤ.አ) የዓለም ዋንጫ ፊፋ እና ዩኒሴፍ “say yes to children” በሚል መሪ ሀሳብ የሕፃናትን መብት ለማስጠበቅ አብረው በዘመቻ መሥራታቸውን መረጃዎች ያሳያሉ። እንደ መረጃው ከሆነ በዘመቻው ለሕፃናት ተስማሚ የሆነች ዓለም ለመገንባት ታስቦ ነው። የሕፃናትን መብት ዘመቻ ማስተዋወቅ፣ የስፖርታዊ ጨዋነትን ማስፈን፣ የሕፃናትን ህልም ማሳካት እና በተለይ ለአካል ጉዳተኞች ደግሞ ሁሉም ከጎናቸው እንደሆኑ ድጋፋቸውን ማሳየት ነው ሁለቱ ተቋማት የተስማሙት። ታዲያ ይህን የተረዱት በርካታ የአውሮፓ ክለቦች አጋጣሚውን ለበጎ አድራጎት ሥራ እየተጠቀሙበት ሲሆን፣ በተለይም የአዕምሮ ውስንነት ያለባቸው፣ አካል ጉዳተኞች እና በተለይም ይህ ደግሞ ለሕሙማን ህፃናት ገደብ የሌለው ደስታ እና ተስፋን እንዲሰንቁ እየተጠቀሙበት ይገኛሉ፡፡
እ.ኤ.አ ከ2002 ጀምሮ የዓለም ዋንጫ ወይም የአውሮፓ ሻምፒዮና አጃቢ አዳጊዎች የሚመረጡት የዝግጅቱ ስፖንሰር በሆነው ማክዶናልድ ባዘጋጀው ውድድር ነው። በተመሳሳይ እ.ኤ.አ በ2014 በብራዚል በተደረገው የዓለም ዋንጫ ዓለም አቀፉ ማክዶናልድ ድርጅት ከ70 የተለያዩ አገራት የተመረጡ 1 ሺህ 408 ሕፃናትን ወጪ በመሸፈን አዳጊዎች የተጫዋች አጃቢ ሆነው በእያንዳንዱ ጨዋታ እንዲገቡ አድርጓል።
እ.ኤ.አ በ2014 ዘጋርዲያን ባወጣው ጥናት አንዳንድ ጊዜም እንደ እንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ያሉ አንዳንዶቹ ክለቦች የተጫዋቾች አጃቢ የሚኖራቸው ሲሆን፣ ለዚህም ከ450 እስከ 600 ፓውንድ ገንዘብ ያስከፍላሉ። ለአዳጊዎችም ክለቡ ሙሉ መስተንግዶ፣ ነፃ የስቴዲየም መግቢያ ትኬት፣ የተጫዋቾች ፊርማ ያረፈበት ኳስ እና ሌሎች ተጨማሪ ስጦታዎች ይበረከትላቸዋል። የተወሰኑ ክለቦችም ተግባሩን ለበጎ አድራጎት ድርጅቶች ነፃ ቦታዎችን ሲሰጡ እና አንዳንዶቹም ክለቦች ያለምንም ክፍያ አዳጊዎች ከተጫዋቾች ጋር ወደሜዳ እንዲገቡ ያደርጋሉ፡፡
በአንዳንድ አጋጣሚዎችም ልዩ አጃቢዎች ሊኖሩ ይችላሉ። ለምሳሌ የአያክስ እግር ኳስ ክለብ ተጫዋቾች ከእናቶቻቸው ጋር በእናቶች ቀን ተያይዘው ሲወጡ በሳኦ ፓውሎ እግር ኳስ ክለብ እንደዚሁ ተጫዋቾች ባለቤት አልባ ውሾች ላይ የሚደርሰውን አካላዊ ጥቃት ለመከላከል እና ግንዛቤ ለመፍጠር ከውሾች ጋር አብረው ወደ ሜዳ የገቡበት አጋጣሚ ተፈጥሯል፡፡
እንደ እንግሊዛዊው ዋይኒ ሩኒ ያሉ አንዳንድ ታዋቂ እግር ኳስ ተጫዋቾች በልጅነታቸው የተጫዋች አጃቢዎች ነበሩ። ለአብነት በ1996 እ.ኤ.አ በመርሲሳይድ ደርቢ ሊቨርፑል እና ኤቨርተን በተጫወቱበት ጊዜ የቀድሞው የማንቸስተር ዩናይትዱ ተጫዋች ዋይኒ ሩኒ ለኤቨርተን ቡድን አጃቢ በመሆን ወደ ሜዳ ገብቶ ነበር። በአዳጊነት ዘመኑ የተጫዋቾች አጃቢ የነበረው ዋይኒ ሩኒ በመጨረሻ ህልሙን አሳክቶ ኮከብ ተጫዋች ለመሆን በቅቷል። ተጫዋቹም በአንድ ወቅት ለመገናኛ ብዙሃን በሰጠው አስተያየት እነዛ የልጅነት አጋጣሚዎች ሲያድግ ህልሙን እንዲኖር እንደረዱት ተናግሮ ነበር፡፡
በአንድ ወቅት የእግር ኳስ ቤተሰቡ ተመለክቷቸው በህሊናው ካሰቀራቸው አስገራሚ ታሪኮች መካከል አንዱ የሆነውን ታሪክ አቅርበን ጽሑፋችንን እንቋጭ፡፡ የእንግሊዙ እግር ኳስ ክለብ ሰንደርላንድ ደጋፊውና የተጫዋች አጃቢ የነበረው የሕፃን ብራድሌይ ሎሪ በወቅቱ የስድስት ዓመት ሕጻን እያለ ነበር ከክለቡ ተጫዋቾች ጋር ወደሜዳ ይገባ የነበረው። የሰንደርላንድ እግር ኳስ ክለብ ቀንደኛ ደጋፊ የነበረና ስሙ በክለቡ የክብር መዝገብ የሰፈረው አዳጊው ብራድሊ በክለቡ የቡድን አባላት እጅግ የሚወደድ ነበር ይላል ታሪኩን ያስነበበው ዘጋርዲያን በዘገባው፡፡
በተለይ ደግሞ ከቀድሞው እንግሊዛዊ የክለቡ ተጫዋች ጀርሜን ዴፎ ጋር የጠበቀ ግንኙነት የነበረው ብራድሌይ ሎሪ ለበርካታ ጊዜያት የተጫዋቾች አጃቢ በመሆን ወደ ሜዳ ገብቷል። በተለይ ደግሞ በ2013 እ.ኤ.አ የካንሰር ታማሚ ከሆነ በኋላ ክለቡ እና ቤተሰቦቹ በምድር ላይ ያለውን ቀሪ ዕድሜ በሚወደው እግር ኳስ እንዲያጣጥም አድርገዋል። በየጨዋታውም የሰንደርላንድን ተጫዋቾች በማጀብ ወደ ሜዳ ይገባ ነበር። ሕፃን ልጃቸው በታህሳስ 2016 ህይወቱ እንደሚያልፍ በዶክተሮች የተነገራቸው ቤተሰቦቹ በቀረችው አጭር ጊዜ ህልሙን እንዲያሳካ አድርገዋል። ሰንደርላንድ እግር ኳስን ለበጎ ኃይል በመጠቀም ለሌሎች አርዓያ የሚሆን ሥራ ሰርቶ አሳይቷል ተብሏል።
በሳህሉ ብርሃኑ