AMN – የካቲት 23/2017 ዓ.ም
የአድዋ ድል ለመላው አፍሪካውያን የነጻነት ተስፋን ያሳየ፣ ቅኝ ገዢዎች ሊያጠፉት የሞከሩትን ሰብዓዊ ክብርን የመለሰ፣ የኢትዮጵያውያንን ጀግንነት እና አይበገሬነትን ያሳየ መሆኑን ፕሬዝዳንት ታየ አጽቀስላሴ ተናገሩ።
129ኛው የአድዋ ድል በዓል ” አድዋ የጥቁር ህዝቦች ድል” በሚል መሪ ቃል ተከብሯል።
በዓሉን በማስመልከት በሚኒሊክ አደባባይ እና በአድዋ ጀግኖች ሀውልት የአበባ ጉንጉን ያስቀመጡት ፕሬዝዳንት ታየ የአድዋ ድል መነሻ የኢትዮጵያዊነት እሳቤ ነው ብለዋል።
የእውቀት እና የሀሳብ ትግል በኢትዮጵያዊ ብሒል ፣ ኢትዮጵያዊ ሀሳብ እና ኢትዮጵያዊ ፍልስፍና ተቀናጅተው ድሉ እንዲገኝ ማድረጋቸውንም ነው ፕሬዝዳንቱ የገለጹት።
አድዋ የአንድ ወቅት ድል ብቻ ሳይሆን ትላንትን የበየነ እና ነገን የተለመ ጭምር ነው ብለዋል ፕሬዝዳንት ታየ አጽቀስላሴ።

በፈተናዎች መሀልም ቢሆን ያልተቆራረጠ እና ለዘመናት የቆየ ስርዓተ መንግስት ያለን መሆናችን ፣ በሰው ልጆች እኩልነት የምናምን እና የቀለም እና የዘር ልዩነትን ህሊናችን የማይቀበል ህዝቦች መሆናችን፣ እንደ ህዝብ ለነጻነታችን የምንሰጠው ፋይዳና እንደ ሰው ለሌሎች ህዝቦች የምንሰጠው ክብር ለአድዋ ድል መደላድል ፈጥረዋል ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ።
የኢትዮጵያውያን አንድነት ፣ ወታደራዊ ብቃት እና ይቅር ባይነት በአድዋ የተገለጠ እና አሁንም ያለ ነው ያሉት ፕሬዝዳንት ታየ የአድዋ አሸናፊነት መንፈስ በመላው አለም ፍትህ እና ነጻነትን ለተጠሙ ህዝቦች የትግል ነጸብራቅ መሆኑንም አንስተዋል።
በግላዊ ቅሬታዎች የሀገር ጉዳይ ቸል እንደማይባል የጠቀሱት ፕሬዝዳንት ታየ አንድነታችን በእኩልነት እና በነጻነት እንዲሁም በእድገት ለመዝለቅ ወሳኝ ነው ብለዋል።
ወጣቱ ትውልድ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለአለም ሰላም ፣ እድገትና ዘመናዊነት የሚተጋ ሊሆን ይገባዋል ያሉት ፕሬዝዳንቱ በእውነት እና ነጻነት መንገድ የአድዋን መንፈስ ሊያስቀጥል እንደሚገባም ነው የተናገሩት።
በሰብስቤ ባዩ