
AMN – ህዳር 2/2017 ዓ.ም
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በተለያዩ ክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች የአጀንዳ ማሰባሰብ ምክክር ምዕራፎች ሲያከናውን መቆየቱ የሚታወስ ነው፡፡
በዚህ ሂደት ኮሚሽኑ አጀንዳን ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት መሰብሰብ ተቀዳሚ ግቡ ሲሆን፤ ሂደቱም ለሀገራዊ ምክክሩ ምዕራፍ ቀጥተኛ ያልሆነ በጎ አስተዋፅኦን በማበርከት ላይ ይገኛል፡፡
ከዚህ በታች የተዘረዘሩት ሀሳቦች ኮሚሽኑ በሂደቱ እያስመዘገባቸው ያሉ ቀጥተኛ ያልሆኑ ውጤቶች ናቸው፡፡
1. በባለድርሻ አካላት መካከል የተሻለ መተማመን እና ግንኙነትን ማዳበር
እየተከናወነ ባለው የአጀንዳ ማሰባሰብ ምክክር ምዕራፍ በሀገራቸው ጉዳይ ላይ መሳተፍ የሚገባቸው ባለድርሻ አካላት ተገናኝተው በጋራ ጉዳዮቻቸው ላይ እየመከሩ ይገኛሉ፡፡
ውይይቶቹ በተለያየ ፈርጆች በተለዩ ወገኖቻችን መካከል መተማመንን በመገንባት ተስፋ ሰጪ የሆኑ በጋራ የመስራት ልምምዶች እንዲዳብሩ አስችለዋል፡፡
2. የባለድርሻ አካላት ባለቤትነትን መፍጠር
የሀገራዊ ምክክር ሁሉም ባለድርሻ አካላት ባለቤትነት ተሰምቷቸው በሂደቱ በእኩል ሊሳተፉበት የሚገባ የዲሞክራሲ ሂደት ነው፡፡
ሂደቱ በተከናወነባቸው የሀገራችን አካባቢዎች የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ለሂደቱ ስኬት በተለያየ ረገድ ያሳዩት ርብርብ እና ተነሳሽነት ይበል የሚያሰኝ ሲሆን ይህም በሂደቱ ያላቸውን ባለቤትነት እንዲገነቡ አስችሏቸዋል፡፡
3. የምክክር ባህልን ማጎልበት
የአጀንዳ ማሰባሰብ በተከናወነባቸው የተለያዩ የሀገራችን አካባቢዎች ግጭቶችን ሀገር በቀል በሆኑ መንገዶች መፍታት የተለመደ እንደሆነ ይታወቃል፡፡
ሆኖም ግን በሀገር በቀል የሽምግልና ስርዓት ያልተፈቱ የሀሳብ ልዩነቶችን ለመፍታት ሂደቱ ሀሳቦች በሚገባ እንዲንሸራሸሩ መንገዱን አመቻችቷል፡፡
ይህም የሀሳብ ልዩነት ያላቸው የተለያዩ ጎራዎች በሀሳብ ልዩነቶቻቸው ላይ ተወያይተው የምክክርን ባህል እንዲያጎለብቱ አጋጣሚ ፈጥሯል፡፡
4. መረጃዎችን ማሰባሰብ
የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ምዕራፍ በርካታ የሚባሉ ባለድርሻ አካላትን ማሳተፉ እሙን ነው፡፡
በሂደቱ ኮሚሽኑ ለስትራቴጂያዊ ጉዳዮች ፍጆታ የሚውሉ እና በቀጣይ ለሚደረጉ የምክክር ሂደቶች ግብዓት የሚሆኑ መረጃዎችን በማሰባሰብ እና በማደራጀት ስኬታማ የሆኑ ተግባራትን ማከናወኑን ከኮሚሽኑ ያገኘነው መረጃ አመላክቷል፡፡