AMN – የካቲት 9/2017 ዓ.ም
የአፍሪካን ብልጽግና እውን ለማድረግ ፍትሕዊ የትምህርት ጥራትና ተደራሽነት ላይ በቁርጠኝነት መስራት እንደሚያስፈልግ የሞሪታኒያ የውጭ ጉዳይና ትብብር ሚኒስትር ሞሃመድ ሳሌም(ዶ/ር) ገለጹ።
በአፍሪካ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ለትምህርት ጥራትና ክህሎት ልማት ዘላቂነት መረጋገጥ የፋይናንስ ድጋፍና ተደራሽነት ላይ ሊወሰዱ በሚገባቸው እርምጃዎች ላይ ያተኮረ ውይይት ተካሂዷል።
በዚሁ ጊዜ የሞሪታኒያ የውጭ ጉዳይና ትብብር ሚኒስትር ሞሃመድ ሳሌም(ዶ/ር)፥ በትምህርት ጥራትና ተደራሽነት ላይ ያለው ውስንነት ህፃናትን ከትምህርት ገበታ ውጪ እንዲሆኑ እያደረገ ነው ብለዋል።
ለዚህም የአህጉሪቱን ህፃናት እና የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ጥራት ያለው የትምህርት ሥርዓት መፍጠር አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።
በአጀንዳ 2063 የበለጸገች አፍሪካን እውን ለማድረግም የትምህርት ጥራትና ፍትሕዊ ተደራሽነትን ማረጋገጥ መሰረታዊ ጉዳይ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።
ትምህርት የአህጉሪቷ ዕድገት መሰረት ነው ያሉት ዶክተር ሞሀመድ ሳሌም፥ የአፍሪካ ሀገራትም የሕብረቱን የ2063 አጀንዳዎች ለማሳካት በሥርዓተ ትምህርት ጥራትና ተደራሽነት ላይ በትብብርና ቁርጠኝነት ልንሰራ ይገባል ብለዋል።

የአፍሪካ ሕብረት የትምህርት፣ ሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ፈጠራ ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መሀመድ በልሆሰኒ በበኩላቸው፥ በተሻለ የትምህርት ሥርዓት የሚገኝ ዕውቀት፣ ፈጠራና ክህሎት ለአህጉሪቷ ዕድገት አስፈላጊ መሆናቸውን አስረድተዋል።
አህጉሪቷ የሰነቀችውን የልማት ግብ እውን ለማድረግም ሀገራት ፍትሕዊ የትምህርት ጥራትና ተደራሽነት ላይ በትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የመንግስታቱ ድርጅት የህፃናት አድን ድርጅት (ዩኒሴፍ) የምስራቅና ደቡብ አፍሪካ ቀጣናዊ ዳይሬክተር ኢተሌቫ ካዲሊ፥ በአህጉሪቱ ፍትሕዊ የትምህርት ጥራትና ተደራሽነትን ለማሻሻል እየተሰራ ቢሆንም ቀጣይነት ያለው ስራ ይጠይቃል ብለዋል።
ዩኒሴፍ የአህጉሪቱን የትምህርት ሥርዓት ለማሻሻል በሚደረገው ጥረት ከመንግስት፣ ከአጋር አካላትና ከማህበረሰቡ ጋር በመተባበር የበኩሉን ኃላፊነት እየተወጣ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በቀጣይም ለአህጉሪቱ ህፃናት ፍትሀዊና ጥራት ያለው ትምህርትን ተደራሽ ለማድረግ እየተከናወኑ ላሉ ጥረቶች የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ማረጋገጣቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
“የማካካሻ ፍትህ ለአፍሪካውያን እና ለዘርዓ አፍሪካውያን” በሚል መሪ ሀሳብ ትላንት የተጀመረው 38ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ በሕብረቱ ዋና መስሪያ ቤት ዛሬም ቀጥሎ እየተካሄደ ይገኛል።