AMN – የካቲት 9/2017 ዓ.ም
የአፍሪካ ህብረት በአህጉሪቱ ግጭት እና አለመረጋጋት ባለባቸው ሀገራት ችግሮችን በንግግር እና በድርድር ለመፍታትና ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ለማድረግ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ የአፍሪካ ህብረት የፖለቲካ ጉዳዮች ፣ የሰላም እና ጸጥታ ኮሚሽነር ባንኮሌ አድገቦዬጋ አድኦዬ ተናገሩ።
ኮሚሽነሩ ከ38ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ጎን ለጎን በአህጉሪቱ የሰላምና ጸጥታ ጉዳዮች ዙሪያ መግለጫ ሰጥተዋል።
በሶማሊያ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ከአፍሪካ ህብረት የሶማሊያ ተልዕኮ (AMISOM) ወደ አፍሪካ ህብረት የሶማሊያ የሽግግር ተልዕኮ (ATMIS) የተደረገው ሽግግር ሁሉንም አካላት ባካተተ ውይይት በሰላማዊ መንገድ እንዲከናወን ትኩረት ሰጥቶ መስራቱን ኮሚሽነሩ ተናግረዋል።
በምስራቃዊ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በምክክር ማዕቀፍ መረጋጋት እንዲመጣ የአፍሪካ ህብረት ትኩረት ሰጥቶ ይሰራል ያሉት ኮሚሽነሩ ከምስራቅ አፍሪካ እና ደቡባዊ አፍሪካ ቀጠናዊ ተቋማት ጋር በሀገሪቱ ሰላምን ለማስፈን እንደሚሰራም ገልጸዋል።

የቅጥረኛ ተዋጊዎች እንቅስቃሴ በሀገሪቱ ላለው ግጭት መባባስ አስተዋጽኦ ያለው በመሆኑ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋትን ለማምጣት ይህን መሰሉ እንቅስቃሴ ሊገታ ይገባልም ብለዋል።
በሱዳን ያለውን ጦርነት ለማስቆም እና ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን የሀገሪቱን ልሂቃን፣ የፖለቲካ እና የጦር ሀይሎች ያካተተ በራሳቸው በሱዳናውያን የሚመራ የፖለቲካ ውይይት ያስፈልጋል ብሎ ህብረቱ ያምናል ብለዋል ኮሚሽነሩ።
ግጭቶችን ተከትሎ የሚፈፀሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ተቀባይነት የላቸውም ያሉት ኮሚሽነሩ አካታች እና አፋጣኝ የተኩስ አቁም ሊደረግ ይገባልም ብለዋል።
10 የሚደርሱ የሊቢያ የፖለቲካ ሀይሎች የፖለቲካ ድርድር ስምምነት ላይ መድረሳቸው በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላምን ለማምጣት ያግዛል ብሎ የአፍሪካ ህብረት ያምናልም ብለዋል።
በአፍሪካ ግጭቶችን ለማስወገድ እና ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን አፍሪካዊ መፍትሄ ለአፍሪካዊ ችግሮች በሚለው መርህ ህብረቱ በጽኑ ያምናል ያሉት ኮሚሽነሩ በዚህም የሰሜን ኢትዮጵያን ግጭት ለማስቆም ከተካሄደው የፕሪቶርያ ስምምነት ብዙ ትምህርት አግኝተናል ይህንኑ አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል።
በሰብስቤ ባዩ