የአፍሪካ ህብረት የሰላም እና ደህንነት ምክር ቤት አዲስ ተመራጭ ሀገራት አባልነታቸውን በይፋ ይረከባሉ

You are currently viewing የአፍሪካ ህብረት የሰላም እና ደህንነት ምክር ቤት አዲስ ተመራጭ ሀገራት አባልነታቸውን በይፋ ይረከባሉ

AMN – መጋቢት 16/2017 ዓ/ም

ኢትዮጵያን ጨምሮ የአፍሪካ ህብረት የሰላም እና ደህንነት ምክር ቤት አዲስ አባላት ከተሰናባች ሀገራት ቦታቸውን የሚረከቡበት ስነ ስርዓት ዛሬ በታንዛንያ አሩሻ መካሄድ ጀምሯል።

የአፍሪካ ህብረት የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት በየካቲት ወር 2017 ዓ.ም ባደረገው 46ኛ መደበኛ ስብስባ፣ አራት የህብረቱን የሰላም እና ደህንነት ምክር ቤት አባላት መምረጡ ይታወቃል።

በዚህም ኢትዮጵያ ከምስራቅ አፍሪካ፣ እስዋቲኒ ከደቡባዊ አፍሪካ፣ ካሜሮን ከማዕከላዊ አፍሪካ እና ናይጄሪያ ከምዕራብ አፍሪካ አባል ሆነው መመረጣቸው የሚታወስ ነው።

ኢትዮጵያ የአፍሪካ ሕብረት የሰላም እና ደህንነት ምክር ቤት ከፈረንጆቹ 2025 እስከ 2027 የቆይታ ዘመን አባል ሆና ተመርጣለች።

በታንዛንያ አሩሻ በተጀመረው የአዲስ ምክር ቤት አባላት የትውውቅ መርሃ ግብር ሀገራቱ ከተሰናባች አባል ሀገራት ቦታቸውን እንደሚረከቡ ኢዜአ ዘግቧል።

ጅቡቲ፣ ናምቢያ እና ሞሮኮ ተሳናባች የምክር ቤቱ አባል ሀገራት ናቸው።

የማስተዋወቂያ መርሃ ግብሩ በይፋዊ የአባልነት ርክክቡ አዲስ ሀገራት ስለ ምክር ቤቱ የስራ ኃላፊነት፣ ተግባራት እና የአሰራር ማዕቀፎች በሚገባ ተረድተው እንዲሰሩ የማድረግ አላማ ያለው ነው።

በሁነቱ የልምምድ ልውውጥ መድረግ እንደተዘጋጀም ለማወቅ ተችሏል።

መርሃ ግብሩ እስከ መጋቢት 18 ቀን 2017 ዓ.ም ይቆያል።

አንጎላ፣ ቦትስዋና፣ ኮትዲቯር፣ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ ግብጽ፣ ኢኳቶሪያል ጊኒ፣ ጋምቢያ፣ ሴራሊዮን፣ ታንዛንያ እና ዩጋንዳ የወቅቱ የምክር ቤቱ አባል ሀገራት ናቸው።

21 ዓመታትን ያስቆጠረው የአፍሪካ ህብረት የሰላም እና ደህንነት ምክር ቤት በአህጉሪቷ ግጭቶች እንዳይከሰቱ አስቀድሞ መከላከል፣ የግጭት አስተዳደርና አፈታት ላይ ከፍተኛ የውሳኔ ሰጪ አካል ነው።

በአህጉሪቷ ለሚከሰቱ ግጭቶች ጊዜውን የጠበቀ እና በቂ ምላሽና ቅድመ ማስጠንቀቂያ ይሰጣል። ለአፍሪካ የሰላም እና ደህንነት ማዕቀፍ ቁልፍ ምሰሶ ነው።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review