የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር እጩዎች የምርጫ ክርክር አካሄዱ

You are currently viewing የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር እጩዎች የምርጫ ክርክር አካሄዱ

AMN – ታኀሣሥ 4/2017 ዓ.ም

የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር እጩዎች የምርጫ ክርክራቸውን ዛሬ ማምሻውን በሕብረቱ መሰብሰቢያ አዳራሽ አካሂደዋል።

የአፍሪካ አንድነት፣ ሰላምና ደህንነት፣ አህጉራዊ የንግድ ትስስርን ማጎልበት፣ ኢኮኖሚ፣ የአፍሪካን ተሰሚነት በዓለም መድረክ መጨመር፣ ተቋማዊ ሪፎርም እና የዜጎች በተለይም የወጣቶች ፍትሐዊ ተጠቃሚነት በክርክሩ ትኩረት የተደረገባቸው ዋንኛ አጀንዳዎች ናቸው።

ክርክሩን ያደረጉት የጅቡቲ የውጭ ጉዳዮች እና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር መሐሙድ አሊ የሱፍ፣ የኬንያ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ራይላ ኦዲንጋ እና የማዳጋስካር የቀድሞ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሪቻርድ ራንድሪያማንድራቶ ናቸው።

እጩዎቹ ለሁለት ሰዓታት በዘለቀው ክርክራቸው ቢመረጡ ሊፈጽሟቸው ያቀዷቸውን እቅዶች በዝርዝር አስረድተዋል።

የጅቡቲ የውጭ ጉዳዮች እና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር መሐሙድ አሊ የሱፍ የኮሚሽኑ ሊቀ መንበር ሆነው ቢመረጡ በሰላም እና ደህንነት በልዩ ትኩረት እንደሚሰሩ ገልጸዋል።

የአፍሪካ ሕዝብ አብዛኛውን ድርሻ የሚይዘውን ወጣት ተጠቃሚ የሚያደርጉ ፕሮጀክቶችንም እንደሚተገብሩ ተናግረዋል።

የኮሚሽኑ ሊቀመንበር ሆኜ ብመረጥ አፍሪካ በዓለም አቀፍ መድረክ ያላትን ተሰሚነት ለማሳደግ እሰራለሁ ብለዋል።

ሌላኛው እጩ የኬንያ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ራይላ ኦዲንጋ የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽነር ሆነው ቢመረጡ የሕብረቱ መስራች አባቶች ሕልም የሆነውን አፍሪካን አንድ የማድረግ ውጥን ማሳካት ዋነኛ ትኩረታቸው እንደሚሆን ገልጸዋል።

በትምህርት፣ በጤና፣ በምርቶች እሴት መጨመር እና በተለያዩ ቁልፍ መስኮች እድገት ላይ በትኩረት እሰራለሁ ብለዋል።

የአፍሪካን የእርስ በእርስ የንግድ ምጣኔና የመሰረተ ልማት ግንባታ ፕሮጀክቶችን የማስፋፋት እቅድ እንዳላቸው ገልጸዋል።

የማዳጋስካር የቀድሞ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሪቻርድ ራንድሪያማንድራቶ የኮሚሽኑ ሊቀመንበር ሆነው ቢመረጡ አካታች የፋይናንስ ተደራሽነት እንዲፈጠርና የዜጎች ፍትሐዊ ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ በትኩረት እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

የአፍሪካንና የሀገራትን ጥቅል ዓመታዊ የኢኮኖሚ እድገት የሚያሳድጉ የአሰራር ማዕቀፎችን እንደሚዘረጉም አመልክተዋል።

የአፍሪካ ሕብረት ተቋማዊ አቅም በማጎልበት የውሳኔ ሰጪነት እና ተወዳዳሪነት አቅሙን ለማሳደግ እሰራለሁ ብለዋል።

የሊቀመንበርነት ምርጫው የካቲት 8 እና 9 ቀን 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ በሚካሄደው 38ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባዔ ላይ ይከናወናል። የዘንድሮው የሕብረቱ ኮሚሽኑ ሊቀ መንበር ከምስራቅ አፍሪካ ቀጣና እንደሚመረጥ ይታወቃል።

ከእ.አ.አ 2017 አንስቶ የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሆነው እያገለገሉ የሚገኙት የ64 ዓመቱ የቻድ ፖለቲከኛና ዲፕሎማት ሙሳ ፋቂ ማህማት የስልጣን ጊዜያቸው በቅርቡ እንደሚጠናቀቅ ኢዜአ ዘግቧል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review