AMN- ጥቅምት 30/2017 ዓ.ም
የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና የአህጉሪቷን ዘላቂ እድገት የሚያረጋግጥና ወደ ብልፅግና የሚያሻግር በመሆኑ ለተግባራዊነቱ መረባረብ እንደሚገባ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ ገለጹ።
15ኛው የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና የንግድ ሚኒስትሮች ጉባዔ በአፍሪካ ህብረት እየተካሄደ ነው።
በመድረኩ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴን ጨምሮ የአፍሪካ የንግድ ሚኒስትሮችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ በዚህ ወቅት፤ የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና የጋራ ራዕያችንን የምናሳካበት የበለጸገች አፍሪካን እውን የምናደርግበት ነው ብለዋል።
የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ንግድና ኢንቨስትመንትን በማሳደግ አህጉራዊ ትስስርና ትብብር የሚፈጥር መሆኑንም ገልጸዋል።
ነፃ የንግድ ቀጣናውን ገቢራዊ ለማድረግ ውይይት ሲደረግ መቆየቱን ገልጸው፣ በፍጥነት ተግባራዊ በማድረግ ቀጣናዊ ትስስሩን ማቀላጠፍ ይገባል ብለዋል።
የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ከንግድ ቀጣናነት ባለፈ የአፍሪካ ዘላቂ እድገት ማረጋገጫ መሆኑን ገልጸዋል።
እንደ አህጉር 1 ነጥብ 4 ቢሊየን አፍሪካውያንን የበለጠ በማስተሳሰር ፈጣንና ወደ ብልፅግና የሚያሻግር ኢኮኖሚያዊ እድገት ማረጋገጥ ያስችላል ብለዋል።
የአፍሪካ ህብረት አጀንዳ 2063 እና የዘላቂ ልማት ግቦችን ለማሳካት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እና ድህነትን ለመቀነስ ወሳኝ መሆኑንም ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ ሁለተኛውን የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ እና የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ በማድረግ ለውጭ ኢንቨስተሮች ምቹ ሁኔታ ፈጥራለች ብለዋል።
ይሄውም የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣናን ትግበራ ለማቀላጠፍ ወሳኝ እርምጃ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ፅህፈት ቤት ዋና ጸሀፊ ዋምኬሌ ሜኔ
የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣናን በብሔራዊ ደረጃ ትግበራውን ማቀላጠፍ ይገባል ብለዋል።
የግሉን ዘርፍ ተዋንያን በማሳተፍ የዲጅታል ንግድን ማቀላጠፍ አስፈላጊ መሆኑንም ነው ያነሱት።
የአፍሪካን ምርትና ምርታማነት በማሻሻል በአፍሪካውያን መካከል ያለውን ንግድ በእጥፍ ወይም ከዚያም በላይ ማሳደግ ይገባል ብለዋል።
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) በበኩላችው፣ አፍሪካውያን ያላቸውን እምቅ አቅም በትብብር መጠቀም የሚገባቸው ወቅት መሆኑን ተናግረዋል።
ነፃ የንግድ ቀጣናው በአፍሪካውያን መካከል ያለውን የንግድ ትስስር በማሳደግ የተሳለጠ ንግድና ኢንቨስትመንትን ለመፍጠር የሚያስችል መሆኑንም ገልጸዋል።
የግሉን ዘርፍ በማነቃቃት ከፍተኛ የሥራ እድል እንደሚፈጥር ገልጸው፣ ለነፃ የንግድ ቀጣናው ውጤታማ ትግበራ ኢትዮጵያ በንቃት እየተሳተፈች መሆኑን ገልጸዋል።
የፓን አፍሪካ መሰረተ ልማት ጥራት ተቋማት ሊቀመንበር ሄንሪ ሮቺ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና በተሟላ ሁኔታ ለመተግበር ጥራት ያለው መሰረተ ልማት መዘርጋት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
በቀጣናው ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ተወዳዳሪ ለመሆን ጥራት ያለው የመሰረተ ልማት ግንባታ ሊኖር ይገባል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡