AMN- ጥቅምት 30/2017 ዓ.ም
የአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ ንግድ ቀጣና የአገልግሎት እና የእቃዎች ንግድ አንድ የጋራ ገበያ ለመፍጠር ከፍተኛ እድል ያመጣ መሆኑን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
15ኛው የአፍሪካ ነጻ ንግድ ቀጣና አባል ሀገራት የንግድ ሚኒስትሮች ጉባኤ በአፍሪካ ሕብረት አዳራሽ በመካሄድ ላይ ይገኛል።
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንዳሉት ጉባኤው አፍሪካን በጋራ ውጤታማ የሚያደርጉ አቅጣጫዎችን ለማመላከት፣ ችግሮችን ለመፍታትና ቁልፍ ጉዳዮች ላይ ለመምከር ያስችላል።
ውይይቱ ምርጥ ተሞክሮዎችን መለዋወጥ እና ወደ ለውጥ የሚያመሩ ተግባራዊ መፍትሔዎችን ለመለየት የሚያግዝ መሆኑን አመልክተዋል።
ኢትዮጵያ የግል ዘርፉን ተሳትፎ፣ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት እና ዲጂታል ትራንስፎርሜሽንን በማበረታታት እድገት ተኮር የኢኮኖሚ ሪፎርም እያካሄደች መሆኑን ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
የአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ ንግድ ቀጣና የአገልግሎት እና የእቃዎች ንግድ አንድ የጋራ ገበያ ለመፍጠር ከፍተኛ እድል ያመጣ መሆኑን ገልጸው በአባል ሃገራት መካከል ንግድን በማሳለጥ፣ ኢንዱስትሪያላይዜሽንን በመገንባት ሰፊ ዕድል የሚፈጥር ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ለሚካሄዱ ማንኛውም ትብብሮች፣ የምግብ ዋስትና መረጋገጥ፣ የኢንዱስትሪያላይዜሽን እና ኢኮኖሚ ግንባታ ላይ ከአባል ሀገራት ጋር በመቆም የበኩሏን እንደምትወጣ መግለጻቸውን ከንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።